SAʴý

ኒካራጓ ኒካራጓ  (ANSA)

የተባበሩት መንግስታት በኒካራጓ እየተከሰቱ ያሉትን አዳዲስ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን አውግዟል

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ቢሮ ባወጣው አዲስ ሪፖርት የኦርቴጋ መንግስት የሃይማኖት ነፃነት ላይ የተጣለውን 'ያልተገባ እገዳ' እንዲሁም የዘፈቀደ እስራት፣ ማስፈራራት፣ በእስር ቤቶች ውስጥ የሚፈጸሙ እንግልቶችን እና በአገሬው ተወላጆች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በመግለጽ አውግዟል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ቢሮ ትናንት ነሃሴ 29 ቀን 2016 ዓ.ም. በጄኔቫ ባወጣው ሪፖርት በኒካራጓ ያለው የሰብአዊ መብት ሁኔታ “በከፋ ሁኔታ እየተባባሰ መጥቷል” ብሏል።

ሪፖርቱ የመካከለኛው አሜሪካ ሀገር በሆነችው ኒካራጓ የደረሰው የሰብአዊ መብት ጥሰት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በዘንድሮ ዓመት ምን ያህል ተባብሶ እንደቀጠለ አፅንዖት ሰጥቶ የገለጸ ሲሆን፥ ሪፖርቱ የዘፈቀደ እስራት፣ የመንግስት ተቺዎችን ማስፈራራት፣ በእስር ቤቶች ውስጥ የሚፈጸሙ እንግልት እና በአገሬው ተወላጆች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች መበራከታቸውን ገልጿል።

አዲስ የወጣው ሪፖርት በመንግስት ተቃዋሚዎች ላይ ወይም “የተለየ ሃሳብ አሏቸው” ተብለው በሚታሰቡ ሰዎች ላይ “የተጠናከረ” እርምጃ እንደሚወሰድባቸው አመልክቷል። ባለሥልጣናቱ የተለየ ሃሳብ ባላቸው ግለሰቦች ላይ ብቻ ሳይሆን ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀሰውን ወይም በመንግሥት ቀጥተኛ ቁጥጥር በማይደረግበት ማንኛውም ሰው ወይም ድርጅት ላይ እያነጣጠሩ እንደሆነ ይገልጻል። ይህ እርምጃ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን፣ ነጻ ሚዲያዎችን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እና ማንኛውንም “ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ ለማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ለውጥ የሚታገሉ አካላት” ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል በማለት ይገልፃል።

እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘገባ ከሆነ ከጥቅምት እስከ ጥር 2016 ዓ.ም. ባሉት ወራት ብቻ 27 ካህናት እና የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች በዘፈቀደ እንደታሰሩ፥ በተጨማሪም 31 የሃይማኖት አባቶች ለተለያዩ ጊዜያት ከታሰሩ በኋላ ከሀገር እንደተባረሩ አመላክቷል።

የኒካራጓ ርዕሰ ከተማ በሆነችው ማናጉዋ የበርካታ የሃይማኖት ድርጅቶችን ህጋዊ ፍቃድ የተሰረዘ ሲሆን፥ ይህም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ላይ የተከፈተው ሰፊ ዘመቻ አካል ነው ተብሏል።

በጄኔቫ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ጽህፈት ቤት በቅርቡ የጸደቀውን የኒካራጓ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ማሻሻያ ላይ ያለውን ስጋት የገለጸ ሲሆን፥ በፕሬዚዳንት ዳንኤል ኦርቴጋ የጸደቀው ህግ የኒካራጓ መንግስት ከሀገር ውጭ በመሆን በመንግስት እና በተቋማቱ ላይ ወይም በህዝብ አስተዳደር ላይ፣ እንዲሁም የሳይበር ወንጀሎችን ጨምሮ
በሃገሪቷ ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች በሚል ክስ የውጭ ዜጎችን ጨምሮ፣ ግለሰቦችን ወይም ድርጅቶችን መክሰስ እንዲችል ይፈቅዳል።

የሪፎርሙ ረቂቅ ህግ ከመጽደቁ ጥቂት ቀደም ብሎ የወጣው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት፥ እንደዚህ አይነት ሰፋፊ ህጎች ጫና ለመፍጠር እና ለማስፈራሪያ ሊውሉ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ቮልከር ቱርክ “መንግስት አስቸኳይ የአካሄድ ለውጥ” እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
 

05 September 2024, 16:03