SAʴý

በቼክ ሪፑብሊክ ነዋሪዎች በጎርፍ የተሞሉ መንገዶችን ሲያቋርጡ በቼክ ሪፑብሊክ ነዋሪዎች በጎርፍ የተሞሉ መንገዶችን ሲያቋርጡ   (AFP or licensors)

የቦሪስ አውሎ ንፋስ እና ከባድ ዝናብ በአውሮፓ ሃገራት ባደረሱት ጉዳት የሟቾች ቁጥር ማሻቀቡ ተነገረ

ቦሪስ በተባለው ማዕበል እና በበርካታ የአውሮጳ ሀገራት ለቀናት በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በደረሰው የጎርፍ አደጋ የሟቾች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ የተነገረ ሲሆን፥ እስካሁን በአደጋው የ14 ሰዎች ህይወት እንዳለፈ እና የነፍስ አድን ሰራተኞች እና ወታደሮች የጉዳት መጠኑን ለመቀነስ በነፍስ አድን ስራ ላይ መሰማራታቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ፖላንድ እና ሮማኒያ በርካታ የሰው ህይወት ያለፈባቸው ሀገራት ሲሆኑ የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ ይችላል ተብሏል።

ከፍተኛው ዝናብ ያስከተለው የወንዞች ውሀ ሙላት፣ ድልድይ እና የመንገድ መሰረተ ልማቶች ላይ ክፉኛ ጉዳት በማድረሱ የነፍስ አድን ሥራውን ፈታኝ እንዳደረገው ተዘግቧል።

የአከባቢው ባለሥልጣናት ሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት አንዳንድ ማህበረሰቦች በአደጋው ምክንያት ለአራት ቀናት ያክል ተገልለው እንደሚገኙ እና ከአርብ ጀምሮ በኦስትሪያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ጀርመን፣ ሃንጋሪ፣ ሮማኒያ እና ስሎቫኪያ ውስጥ ከፍተኛ ንፋስ እና ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ከባድ ዝናብ መጣሉን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በቼክ ሪፐብሊክ ከዋና ከተማዋ 230 ኪሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ከተማ 70 በመቶ በውሀ ተሸፍናለች፣ በዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ የተኛው ውሀም ጥልቀቱ ሁለት ሜትር እንደሚሆን፥ በተለይም በሰሜን ምስራቅ የሚገኙ 119,000 የሚያህሉ አባወራዎች የኤሌክትሪክ ኃይል እንደተቋረጠባቸው የተዘገበ ሲሆን፥ ብዙዎች ከዚህን ቀደም በደረሰው የጎርፍ መጥለቅለቅ የሞቱትን በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎችን አሁንም እንደሚያስታዉሱ ተጠቁሟል።

የፖላንድ መንግስት አደጋው በደረሰባቸው ስፍራዎች የአደጋ ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀ ሲሆን በጎርፉ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለመደገፍ 1 ቢሊየን ዝሎቲ ወይም 260 ሚሊየን ዶላር በጅቷል። በተጨማሪም የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ዶናልድ ተስክ በጎርፍ አደጋው ጉዳት ከደረሰባቸው የጎረቤት ሀገራት ጋር እየተወያዩ እንደሚገኙ እና ከአውሮፓ ህብረት ተጨማሪ የገንዘብ እርዳታ በጋራ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል፡፡

“አደጋው ሁሉንም ነገር አውድሟል፥ ምንም የቀረኝ ነገር የለም” ሲሉ የገለጹት አንዲት ሮማንያናዊት የእድሜ ባለጸጋ፥ “አልጋዎቹ እና ትራሶቹ በጭቃ ተሞልተዋል፣ በዚህም ምክንያት የምተኛበት ቦታ የለኝም፥ ምንም ነገር የለም” ሲሉ በቀደሞው ድህነታቸው ላይ በተጨማሪ ስለተከሰተው አደጋ አስከፊነት ተናግረዋል።

ከሀንጋሪ ሰሜናዊ ምዕራብ አቅጣጫ በዋና ከተማዋ ቡዳፔስትን ጨምሮ በዳኑቤ እና በየመንገዱ ላይ ያሉ ወንዞች ከፍታቸው ሊጨምሩ ስለሚችሉ መንግስት የጎርፍ መከላከያዎችን ለማጠናከር ከ350 በላይ ወታደሮችን አሰማርቷል።

የጎርፍ አደጋ በመካከለኛው እና በምስራቅ አውሮፓ ውስጥ ባሉ ህዝቦች ላይ ያስከተለውን ተጽእኖ በተመለከተ የተለያዩ ክርክሮች ያሉ ሲሆን፥ በርካታ ሳይንቲስቶች ለእነዚህ አደጋዎች የአየር ንብረት ለውጥን እንደምክንያት ሲያቀርቡ፣ ሌሎች ባለሙያዎች ደግሞ በወንዞች አቅራቢያ እየተከናወኑ የሚገኙ መጠነ ሰፊ ግንባታዎችን እና በቂ የሆነ የውሃ አጠቃቀም ቁጥጥር አለመኖሩን በተጠያቂነት ያቀርባሉ።
 

18 September 2024, 14:39