SAʴý

የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት  (AFP or licensors)

በጋዛ በተፈጸመ ድንገተኛ ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተነገረ

እስራኤል በጋዛ ባደረሰችው ድንገተኛ የአየር ጥቃት ቢያንስ 10 ፍልስጤማውያን መሞታቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ይገኛሉ።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የፍልስጤም የዜና ተቋም የሆነው ዋፋ እንደዘገበው እስራኤል በጋዛ ሰርጥ በስተምስራቅ በሚገኙ የመኖሪያ ቤቶች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሟን የገለጸ ሲሆን፥ በጥቃቱ ከተገደሉት መካከል አራት ህጻናት እና ሶስት ሴቶች እንደሚገኙበት እና ሌሎች በርካታ ሰዎች ግን ደብዛቸው እንደጠፋ ዘግቧል።

ታጋቾች እንዲመለሱ የተጠየቀበት ሰልፍ
በሌላ ዜና ደግሞ በእስራኤል እየተደረገ ያለው እና በሃማስ ታጣቂዎች ታግተው የተወሰዱ ታጋቾች እንዲመለሱ የተጠየቀበት ትልቅ ሰላማዊ ሰልፍ ሃገሪቷ ላይ ውጥረት እየጨመረ መምጣቱ ተነግሯል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በጋዛ በሚገኙ የእስራኤል ወታደሮች የስድስት ታጋቾች አስከሬን ከተገኘ በኋላ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመላው እስራኤል ሰልፍ እያካሄዱ የሚገኙ ሲሆን፥ አሁን ባለው ሁኔታ በአጠቃላይ 97 ምርኮኞች እስካሁን የደረሱበት እንዳልታወቀም ተመላክቷል። ይህ አስከፊ ጦርነት ባለፈው ዓመት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ ከ41,000 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ባለስልጣናት እየተናገሩ ይገኛሉ።

እስራኤል በሶሪያ ጥቃት ፈጸመች
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የእስራኤል ልዩ ሃይሎች በሶሪያ ውስጥ በሚገኘው የሄዝቦላ የሚሳኤል ማምረቻ ቦታ ላይ ያደረሱትን ድፍረት የተሞላበት ጥቃት በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎች እየወጡ ሲሆን፥ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያለው የሶሪያ ራዲዮ ጣቢያ ባለፈው ሳምንት በሊባኖስ ድንበር አቅራቢያ በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በማስያፍ ከተማ 18 ሰዎች መገደላቸውን ዘግቧል።

በተጨማሪም ኒውዮርክ ታይምስ እንደዘገበው የእስራኤል ልዩ ሃይሎች ከሄሊኮፕተሮች ላይ በመውረድ የተለያዩ ፈንጂዎችን የሄዝቦላ የሚሳኤል ማምረቻ ተቋም ውስጥ አጥምደው በማፈንዳት ሚስጥራዊ መረጃዎችን ማስወገዳቸውን ገልጿል። ባለፈው ሳምንት የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ሀገሪቱ ወታደራዊ ዘመቻዋን ወደ ሊባኖስ እያዘዋወረች መሆኗን አረጋግጠው እንደነበር አይዘነጋም።

በድንበር አካባቢ ውጥረት ጨምሯል
መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ሃማስ በእስራኤል ላይ የወሰደውን ድንገተኛ ጥቃት በመደገፍ ሄዝቦላህ ወደ እስራኤል ያስወነጨፈውን ሮኬቶችን ተከትሎ እስራኤል በአጸፋው ወደ ደቡብ ምስራቅ ሊባኖስ አከባቢ ላይ ከባድ መሳሪያዎችን በመተኮስ ላይ የምትገኝ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት በሊባኖስና እስራኤል ድንበር ላይ ያለው ውጥረት ተባብሶ መቀጠሉ ተነግሯል።

 

16 September 2024, 17:34