SAʴý

ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን  (ANSA)

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ቅድስት መንበር በተባበሩት መንግስታት መሳተፍ የጀመረችበትን 60ኛ ዓመት አከበሩ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሃፊ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ቅድስት መንበር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ታዛቢ ሃገር ሆና መሳተፍ የጀመረችበትን 60ኛ ዓመት ክብረ በዓል በኒውዮርክ ከተማ ሚድታውን በሚገኘው የቅዱስ ቤተሰብ ቤተ ክርስቲያን መስዋዕተ ቅዳሴ በማሳረግ አክብረዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሃፊ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም. ሰኞ ዕለት በኒውዮርክ ግዛት በሚድታውን ማንሃተን ከተማ በ47ኛው ጎዳና ላይ በሚገኘው የቅዱስ ቤተሰብ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት መንበር በተባበሩት መንግስታት ጉባኤዎች ላይ ቋሚ ታዛቢ ሆና መሳተፍ የጀመረችበትን 60ኛ ዓመት ለማስታወስ መስዋዕተ ቅዳሴ በማሳረግ ዕለቱን አሳልፈዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዕውቅና ከተሰጣቸው የዲፕሎማቲክ ቡድን አባላት እና የቅድስት መንበር የቋሚ ታዛቢ ተልእኮ ወዳጆችን ጨምሮ ለልዩ ዝግጅቱ ከተሰበሰቡት ጋር በመሆን መስዋዕተ ቅዳሴ በማሳረግ የተሰማቸውን ደስታ ሲገልጹ፥ የቅዱስ ቁርባን ሥነ ስርዓት ማለት ‘ምስጋና ማቅረብ’ ማለት እንደሆነ አስታውሰው፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት እራሱን ለእግዚአብሔር እና ለሰው ልጆች ያለስስት እራሱን በስጦታ አሳልፎ የሰጠበትን እና ማለቂያ የሌለው ፍቅሩን ስላሳየን የምናመሰግንበት ሥነ ስርዓት ነው በማለት አስታውሰዋል።

“እኔ አምናለሁ” በማለት የቀጠሉት ብጹእ ካርዲናሉ፥ “እኔንም ጨምሮ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ቅድስት መንበር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ታዛቢ ሃገር ሆና የተገኘችበትን 60ኛ ዓመት ክብረ በዓል አስመልክተው በኒውዮርክ ለሚገኘው የተልዕኮ ቡድን በተለያዩ መንገዶች ለምታደርጉት ወዳጅነት ያስተላለፉትን የምስጋና መልዕክት ለእያንዳንዱ ሰው ለማስተላለፍ እና ለመግለፅ እዚህ ከምናከብረው መስዋዕተ ቅዳሴ የበለጠ የተሻለ አውድ እንደሌለ አምናለሁ” ብለዋል።

የጌታ ግብዣ
ብጹእ ካርዲናል ፓሮሊን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ህዝቡን እንድንጠብቅ፣ እንድንንከባከብ እና እንድናገለግል እንደጠየቀን በማስታወስ፥ “ክርስቲያን መሆን ማለት የወንድሞቻችንን እና የእህቶቻችንን ክብር ከፍ ማድረግ፣ ለዚህም መታገል እና መኖርን ይጠይቃል” ሲሉ በአጽንዖት የገለጹ ሲሆን፥ “በትክክል በዚህ አመክንዮ ለታናናሾች እና ድምጽ ለሌላቸው ሰዎች የማገልገል አመክንዮን እውን ለማድረግ የቅድስት መንበር በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ደረጃ መገኘት አስፈላጊ ነበር” በማለት ቅድስት መንበር በተባበሩት መንግስታት ቋሚ ታዛቢ ሆና የመሳተፏን ጥቅም አብራርተዋል።

ብጹእ ካርዲናሉ ቅድስት መንበር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደ ታዛቢ ሃገር ሆና የዛሬ ስልሳ ዓመታት ከተቀላቀለች በኋላ ሰብዓዊ ክብርን ለማስጠበቅ እና ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር በትጋት ስትሰራ መቆየቷን ጠቁመው፥ “በተለይም የመኖር መብት የሆኑትን በሁሉም መሠረታዊ መብቶች” ላይ አጥብቃ ስትሰራ እንደነበር ገልጸዋል።

ከዚህም በላይ ለማህበራዊ ፍትህ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ብሎም ተሟጋች እና ከለላ የሌላቸውን እና የተረሱትን ለመጠበቅ ያለመታከት መስራቷን ተናግሯል።

የቅድስት መንበር ተልእኮ ቡድን እንደ 'የሰብዓዊነት ተሟጋች'
ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን እ.አ.አ. ጥቅምት 4 ቀን 1965 ዓ.ም. የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኙት እና ንግግር ያደረጉትን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እንደሆኑ ጠቅሰው፥ ብጹእነታቸው በወቅቱ ባደረጉት ንግግር “የቅድስት መንበር ተልእኮ ቡድን የቤተ ክርስቲያንን ጥበብ ‘የሰብአዊነት ተሟጋች’ አድርጎ ያቀርባል” ማለታቸውን አስታውሰዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል ከፈለግን እርሱ ራሱ ያወጣውን መንገድ መከተል አለብን" በማለት፣ መንገዱ ‘የአገልግሎት መንገድ’ መሆኑን አጽንዖት በመስጠት የገለጹ ሲሆን፥ መቀበል የሚያስፈልጋቸውን እና በምላሹ ምንም መስጠት የማይችሉትን ማገልገል አለብን ሲሉ በመጠቆም፥ “የተገለሉትን እና ችላ የተባሉትን ስንቀበል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደተቀበልን ይቆጠራል፣ ምክንያቱም ክርስቶስ እነሱ ውስጥ ይገኛልና” ብለዋል።

ሰላምን እውን ለማድረግ ራሳችንን ደግመን መግለጽ
በመቀጠልም በቤተክርስቲያኑ በኩል በተካሄደው የአቀባበል ሥነ ስርዓት ላይ፣ ብጹእ ካርዲናሉ “በጠባብ ፍላጎቶች እየተከፋፈለ ባለው ዓለም ውስጥ ሁላችንም የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናችንን ማስታወስ አለብን” ሲሉ በድጋሚ ተናግረዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በማስከተልም “ሰላም፣ ፍትህ እና ሰብአዊ ክብር ምኞቶች ብቻ ሳይሆኑ ለሁሉም የሰው ልጅ ተግባራዊ መሆን የሚገባቸው እውነታዎች እንደሆኑ፥ ለዚህም ራሳችንን ሰጥተን መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ፍሬያማ ትብብር ወደ ተሻለ ዓለም ይመራል
ካርዲናሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአባል ሀገራቱን ተወካዮች ለዚህ ዘላቂ ፍሬያማ ትብብር አመስግነው፥ “ቀጣዮቹ 60 ዓመታት እና ከዚያም በኋላ በጋራ እሴቶቻችን እና ለተሻለ ዓለም ባለን የጋራ ተስፋ እየተመራን በጋራ መስራታችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በመጨረሻም ባስተላለፉት መልዕክት ላለፉት ዓመታት የቅድስት መንበር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ መገኘቷን አረጋግጠው፥ “በእምነት እና በምክንያት ላይ የተመሰረተ የፍቅር መልእክት ሲያውጁ ለነበሩ” ለሁሉም ቋሚ ታዛቢዎች እና ተባባሪዎቻቸው ልባዊ ምስጋናቸውን ካቀረቡ በኋላ፥ “በቅዱስ አባታችን ስም እላችኋለሁ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እሳቸውን ወክለን ስለተገኘን ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ” በማለት ተሳታፊዎቹን ለቅዱስ አባታችን ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ‘ጽዋችንን እናንሳ’ በማለት ጋብዘዋል።
 

02 October 2024, 13:44