SAʴý

የጠቅላላ ሲኖዶስ መደበኛ ጉባኤ የጠቅላላ ሲኖዶስ መደበኛ ጉባኤ   (ANSA)

ካርዲናል ግሬሽ፥ ጸሎት እና ለቅድስት ማርያም የሚሰጥ አደራ የሲኖዶሱ ሱባኤ ርዕሦች መሆናቸውን ገለጹ

በቫቲካን ከመስከረም 22 እስከ ጥቅምት 17/2017 ዓ. ም. ሊካሄድ የታቀደው ጠቅላላ የሲኖዶሱ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ ከመከፈቱ በፊት ባሉት ሁለት ቀናት የሚደረገውን ሱባኤ በማስመልከት የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ ቀደም ብለው ለተሳታፊዎቹ ባቀርቡት ማሳሰቢያ፥ የሲኖዶሱ ተሳታፊዎች አስቀድመው የተዘጋጁባቸውን አቀራረቦች እና ዘዴዎች ወደ ጎን በመተው በምትኩ የሁለተኛ ዙር የሲኖዶሳዊ ጉባኤ የማዳመጥ ምሳሌ ለሆነች ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አደራ እንዲሰጡ ጋብዘዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች በሲኖዶሱ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለሚሳተፉት ሰዎች ባቀረቡት የመጀመሪያ ቀን የአቀባበል ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የጸሎትን አስፈላጊነት በመግለጽ፥ የቤተ ክርስቲያን ለውጦች ጸሎት ያልታከሉባቸው ከሆኑ የቡድን ለውጦች ብቻ እንደሚሆኑ እና ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሚሰጥ አደራ ውጭ ከሆነ ቤተ ክርስቲያንም ከድርጅትነት የዘለለ ሌላ ምንም ልትሆን እንደማትችል አስረድተዋል።

የሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ግሬች፥ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን ሁለት ጥቅሶች በቅደም ተከተል በመጥቀስ፥ የመጀመሪያው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና ሁለተኛው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1979 ዓ. ም. ከታተመው የጀርመን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ሠነድ የተወሰደ ትርጉም እና በግልጽ ሊታወስ የሚገባውን ንድፍ፥ ረቡዕ መስከረም 22/2017 ዓ. ም. በይፋ በሚከፈተው የሲኖዶሱ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ዋዜማ ላይ አሰምተዋል።

በተቀደሰ መሬት ላይ
ብፁዕ ካርዲናል ግሬች በዚህ ንግግራቸው፥ የሲኖዶሱ ዋና ተዋናይ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ገልጸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “መንፈስ ቅዱስ ከሌለበት የሲኖዶስ ጉባኤ ሊካሄድ አይችልም” በማለት ደጋግመው የተናገሩትን አስታውሰዋል።

የሙሴን የሲና ተራራ ምስል ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናል ግሬች፥ ሙሴ በተቃጠለው ቁጥቋጦ ፊት እንዳደረገው ሁሉ የሲኖዶሱ ተሳታፊዎችም በቅዱስ ሥፍራ ላይ መገኘታቸውን በትሕትና ሊገነዘቡት ይገባል ብለዋል።

ያልተከፋፈለ ቅርስ
በጌታ ፊት ሙሴ ጫማውን ሲያወልቅ የታየበት ምስል ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናል ግሬች፥ የሲኖዶሱ ተሳታፊዎችም ይህን እንዲያደርጉ ተጠርተዋል ሲሉ አስረድተዋል። “ትላንት ትርጉም የነበራቸው የአቀራረብ እና የሥርዓት መንገዶች ዛሬ ግን ለወንጌል ተልዕኮው ሸክም በመሆን የቤተ ክርስቲያንን ተአማኒነት አደጋ ላይ ጥለዋል” ሲል ተናግረው፥ “ሌላውን ማዳመጥእና በእግዚአብሔር ፊት ራስን ባዶ ማድረግ ሥር ነቀል ተግባር ስለሆነ ይህን ለማድረግ ራሳችንን ፈቃደኞች ማድረግ አለብን” ብለዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግረሽ አክለውም፥ “ምንም እንኳን የሲኖዶሱ ተሳታፊዎች ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት የመጡ፣ ሁሉም የየራሳቸው መንፈሳዊ ሃብት፣ የራሳቸው ተግዳሮቶች፣ ራሳቸውን ማደስ የሚፈልጉ እና ኢየሱስን ለዛሬው ዓለም ለመመስከር አዲስ መንገድ እና አዲስ ቋንቋ ለመፈለግ ቢመጡም፥ በእነዚህ ቀናት ውስጥ የቤተ ክርስቲያኗን መንፈሳዊ እሴቶች ባልተከፋፈለ እና ማንንም ወደ ጎን በማያደርግ የጋራ መንፈስ ለመጋራት ተቀምጠናል” ብለዋል።

የቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ ተግባር
በዚህ አመለካከት እና ስሜት በመጋራት እና በመቀበል፣ ይህንን የጠቅላላ ጉባኤ ወቅት ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥበቃ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ብፁዕ ካርዲናል ግሬች አጽንኦት ሰጥተዋል። “እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔርን ቃል በእምነት የምትቀበል እና የምታዳምጥ ናት” ያሉት ብጹዕነታቸው፥ ይህም ለእርሷ ወደ መለኮታዊ እናትነት የሄደችበት መንገድ መጀመሪያ ነበር” በማለት ከቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያን በመጥቀስ ተናግረዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1979 ይፋ ከሆነው የጀርመን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ሠነድ ላይ የተወሰደውን እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቤልጂየም ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ሲመለሱ አይሮፕላን ውስጥ በሰጡት መግለጫ ለጋዜጠኞች የተናገሩትን እና ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን የበላይነት የሚያስተጋባ መሪ ቃል አስታውሰዋል።

የኢየሱስ እናት እውነተኛ የቤተ ክርስቲያኗን መሠረት እንደሆነች ከዚያ በኋላ የሚመጡት ነገሮች ማለትም ሐዋርያዊ አገልግሎት፣ ቅዱሳት ምስጢራት፣ ለዓለም በሙሉ የሚቀርብ የወንጌል ምስክርነት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መሠረትነት ይገልጻል” ብለዋል።

የመቁጠሪያ ጸሎት የሲኖዶሱ ጸሎት ነው
የሲኖዶሱ ዋና ጸሃፊው በመክፈቻ ንግግራቸው፥ የሲኖዶስ ጉባኤ የእግዚአብሔር ቃል ብዙ ፍሬ የሚያፈራበት መልካም አፈር እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ለእመቤታች ቅድስት ድንግል ማርያም በተሰጠ የጥቅምት ወር ውስጥ የሲኖዶሱ ተሳታፊዎች በሥራቸው ሁሉ በትጋት የመቁጠሪያ ጸሎት እንዲያደርሱ በአደራ አሳስበዋል። በእግዚአብሔርን ቃል ላይ ያለማቋረጥ በማሰላሰል የሲኖዶሱ ተሳታፊዎች በእነዚህ ቀናት ውስጥ በኅብረት በምናደርገው ጉዞ የመቁጠሪያን ጸሎት እንዲያደርሱ በማሳሰብ፥ የመመቁጠሪያ ጸሎት ምስጢር የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት በመከተል ትኩረት በማድረግ እርሱን ለዓለም ማሳየትን እንደሚያረጋግጥ እና በዚህ ጸሎት እንደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የጌታ ደቀ መዛሙርት መሆንን እንማራለን ብለዋል።

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፥ “ዛሬ የሚጀምረው የሲኖዶስ ጉባኤ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የሰውን ልጆች ሕይወት በማዳበር እና በመንፈስ ቅዱስ በማደስ ሲኖዶሳዊ እና ሚሲዮናዊ ቤተ ክርስቲያን እንድንሆን ያስችለናል” ብለዋል።

 

01 October 2024, 17:11