SAʴý

የቪየናው ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) 68ኛ ጠቅላላ ጉባኤ የቪየናው ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) 68ኛ ጠቅላላ ጉባኤ   (AFP or licensors)

ቅድስት መንበር የኒውክሌር መሣሪያዎች ቅነሳ መርሃ-ግብርን እንደምትደግፈው በድጋሚ አስታወቀች

በቅድስት መንበር የአገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ በቪየና ከመስከረም 6-10/2017 ዓ. ም. እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) 68ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር አድርገዋል። ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ በዚህ ንግግራቸው የኒውክሌር መሣሪያዎች ቅነሳ እና የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት ደግፈዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ከመስከረም 6-10/2017 ዓ. ም. በአውስትሪያ መዲና ቪየና እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጉባኤ የመጀመሪያ ቀን ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ከኒውክሌር የጦር መሣሪያ ነፃ የሆነች ዓለምን በመገንባት ረገድ ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) የሚጫወተውን ወሳኝ ሚናን ቅድስት መንበር እንደምትገነዘበው ገልጸው፥ ይህም “የሚቻል እና አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

ለኒውክሌር መሣሪያዎች ቅነሳ ሥርዓት ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ የሚያበረክታቸውን በርካታ አስተዋፅኦዎች እንዲሁም ለኒውክሌር ቴክኖሎጂዎች ደህንነት እና ሰላማዊ አጠቃቀም ለሚያደርገው የማይናወጥ ጥረት ያላቸውን ድጋፍ በድጋሚ ገልጸው፥ የእነዚህ ቴክኖሎጂዎች አገልግሎት ሰጪነት ዘወትር ከሰው ልጅ የጋራ ጥቅም እና ከእያንዳንዱ ሰው ሁለንተናዊ ዕድገት አንፃር መታየት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዛፖሪዢያ እና የከርስክ የኃይል ማመንጫዎች ደህንነት
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ኤጀንሲው ለኒውክሌር ደህንነት ዕድገት ከሚያደርገው አስተዋፅኦ መካከል የኒውክሌር አደጋን ለመከላከል የዛፖሪዢያ እና የከርስክ የኃይል ማመንጫዎች ደህንነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ቅድስት መንበር እንደምትደግፈው አስታውቀዋል።

በተለይ በዛፖሪዢያ እና በከርስክ የኑክሌር ኃይል ማመንጫዎች አቅራቢያ ያሉ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ በዩክሬን ውስጥ ካለው ጦርነት ጋር የተሳሰሩ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እጅግ አሳሳቢ መሆናቸው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ተናግረዋል። የዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) ዋና ዳይሬክተር አቶ ራፋኤል ማሪያኖ ግሮሲ እና የኃይል ማመንጫዎቹ ተቆጣጣሪዎችን ለድፍረታቸው እና ሙያዊ ብቃታቸው እንዲሁም በዛፖሪዢያ በዘላቂነት በመቆየት በሁኔታው ላይ ገለልተኛ እና ተጨባጭ ዘገባዎችን ማቅረብ በመቻልቸው አወድሰው፥ ቅድስት መንበር በግጭቱ ውስጥ ያሉ አካላት በእነዚህ ቦታዎች ላይ ጥቃት ከመፈጸም እንዲቆጠቡ ማሳሰቧን እና መዘዙ በሰው ልጆች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ እና የኢራን-ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ውይይት
ከዓመታት በፊት በጋራ ሁሉን አቀፍ የድርጊት መርሃ ግብር (JCPOA) የኒውክሌር መሣርያዎች ማስፋፊያ ፕሮግራም ስምምነት ተግባራዊነት በመቋረጡ ቅድስት መንበር ብትጸጸትም ነገር ግን ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ከኢራን ጋር በኒውክሌር መርሃ ግብር ጉዳይ ላይ የሚያደርገውን ዘላቂ ጥረት በደስታ ተቀብለዋለች። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ በያዝነው ዓመት ጥር ወር ላይ ለዲፕሎማሲያዊ አካላት ባደረጉት ንግግር፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሁሉን አቀፍ የጋራ ድርጊት መርሃ ግብር “JCPOA”ን ወደነበረበት ለመመለስ ድርድር እንደገና እንደሚጀመር ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ለሁሉም መልካም የወደፊት ዕድል ለማረጋገጥ ያላቸውን ተስፋ አስታውሰዋል። ድርድሮቹ በዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮሪያ (DPRK) የኒውክሌር መርሃ ግብር ጭምር ቅድስት መንበር ተስፋ ያደረገችባቸው እንደሆኑ ሊቀ ጳጳሱ ገልጸው፥ በዚህም ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲው ሰላምን እና ደህንነትን ለማስተዋወቅ፣ እርስ በርስ ከመሟገት ይልቅ የመተማመን መንፈስን ለመገንባት የሚያግዝ ወሳኝ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ አክለው አስታውቀዋል።

 

19 September 2024, 14:40