SAʴý

ብፁዕ ካርዲናል ዘናሪ በሶርያ ደማስቆ በሚገኝ ቅድስት ማርያም የጸጋዎች እናት ቤተ ክርስቲያን መስዋዕተ ቅዳሴን ሲመሩ ብፁዕ ካርዲናል ዘናሪ በሶርያ ደማስቆ በሚገኝ ቅድስት ማርያም የጸጋዎች እናት ቤተ ክርስቲያን መስዋዕተ ቅዳሴን ሲመሩ 

ብፁዕ ካርዲናል ዘናሪ ሶርያ ውስጥ ድህነት ተስፋን እያስቆረጠ እንደሚገኝ ገለጹ

በሶርያ የቅድስት መንበር እንደራሴ ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ፥ የሶርያ ሕዝብ ስቃይ በተጋሩበት ስብከት፥ ሶርያ ውስጥ ድህነት ሕዝብን ተስፋን እያስቆረጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዓለም አቀፉ ዕይታ የወጣች የምትመስል የሶርያን ችግር ዘወትር እንደሚያስታውሱ ይታወቃል። ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ በደማስቆ ስላለው የኢየሱስ ክርስቶስ ጽኑ ምስክርነት እና ለሶርያ ሕዝብ የተስፋ ብርሃን በመሆን በዲያቆንነት በሚያገለግሉበት በቅድስት ማርያም የጸጋዎች እናት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እሁድ መስከረም የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ መርተዋል። ብጹዕነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት እና ከዚያ በኋላ ከምእመናን ጋር ባደረጉት ቆይታ ከአሥር ዓመታት በላይ በዘለቀው ጦርነት ሕዝቡ የደረሰበትን ስቃይ በግልፅ ተናግረዋል።

“ጦርነት ባስከተለው ስቃይ የሶርያ ሕዝብ ደክሟል” ሲሉ በቁጭት የተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ፥የወደፊቱን ብርሃን ለማየት ሕዝብ ትግል ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የተጎጂዎች ብዛት አሳዛኝ እውነታን ይናገራል ያሉት ብጹዕነታቸው፥ በጦርነቱ 500,000 ሕይወት መጥፋቱን፥ ከ7 ሚሊዮን በላይ መፈናቀሉን እና ከ5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ወደ ጎረቤት ሀገራት ለመሰደድ መገደዳቸውን ተናግረዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደገለጸው፥ 16.7 ሚሊዮን ሶርያውያን አስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው እና ወደ 13 ሚሊዮን የሚጠጉት ከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጦት እንዳለባቸው አስታውቋል።

በሌስቦ የሚገኙ የሶርያ ስደተኞች
በሌስቦ የሚገኙ የሶርያ ስደተኞች

በግል እና በጋራ ችግር መካከል ያለውን ተመሳሳይነት የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ፥ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ በሚሸከሙት ትላልቅ እና ትናንሽ መስቀሎች ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አሰምተዋል። ሆኖም በሶርያ ውስጥ የእነዚህ መስቀሎች ክብደት ፈጽሞ የማይገመት ነው ያሉት ብጹ ዕንታቸው፥ ያለፉት ዓመታት አሳዛኝ ትዝታዎችን በተለይም ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሶርያውያን በዝናብ እና በበረዶ ውስጥ ሲራመዱ፣ መሸከም የሚችሉትን ብቻ ይዘው ከአመጽ ሲሸሹ የሚያሳይ ምስል አስታውሰዋል። ከዚያም ሌላ አሳዛኝ ትዝታ ሲያጋሩ፥ በሆምስ ከተማ በስቅለተ ዓርብ ዕለት የሚዘንቡ ቦምቦችን ያስታወሱት ብጹዕነታቸው፥ አንድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ቤተ ክርስቲያናት በወደመበት ሥፍራም ቢሆን ለመስዋዕተ ቅዳሴ የሚሆን ቦታ እንደሚያዘጋጅ መጠየቁን እና በመሃልም የመቃብር ቦታ የሚል ምልክት እንዲያስቀምጥ መታዘዙን አስታውሰዋል።

አሁን ያለውን ሁኔታ በማስታወስ ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ እንደገለጹት፥ አዲስ እና መሰሪ ውድመት በማስከተል ላይ የሚገኘው ድህነት እንደሆነ ገልጸው፥ በኃይለኛው የጦርነት ዓመታት ውድመቶችን፣ ሞትን፣ እጃቸውን እና እግራቸውን የተቆረጡ ሕፃናትን እና ብዙ መከራዎችን መመልከታቸውን ተናግረዋል። አሁን ግን ከቀድሞው የተለየ የድኅነት ቦምብ እንደፈነዳ ገልጸው፥ “ድህነት ለተስፋ ቦታ አይሰጥም” ሲሉ አስረድተዋል። በሶርያ መንግሥት ላይ የተጣለው ዓለም አቀፍ ማዕቀብ በሕዝቡ ላይ አስከፊ ተጽእኖ ማሳደሩን አፅንኦት ሰጥተዋል። “በጦርነቱ ወቅት ቢያንስ ብርሃን ነበረ ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ አሁን ግን ብርሃን ጠፍቶ አገሪቱ ጨለማ ውስጥ እንደገባች ገልጸዋል። የመድሃኒት፣ የምግብ እና የመሠረታዊ ፍላጎቶች እጦት ከተዳከመው የኢኮኖሚ እና የትምህርት ሥርዓት ጋር መባባሱን አስረድተዋል።

በሊባኖስ የሚገኙ የሶርያ ተፈናቃዮች
በሊባኖስ የሚገኙ የሶርያ ተፈናቃዮች

ድህነትን መቋቋም ባለመቻሉ ሁኔታው ብዙዎችን እንዲሰደዱ አድርጓቸዋል ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ፥ “ዛሬ አንድ ዶክተር በወር የሚያገኘው 20 ዩሮ ብቻ እንደሆነ እና ተማሪዎች ትምህርታቸውን የሚከታተሉት ሲችሉ ብቻ እንደሆነ፥ ነገር ግን አእምሯቸው ለዚህ ሳይሆን ለስደት መዘጋጀቱን ገልጸዋል። በዚህ አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን በግንባር ቀደምትነት እንደምትገኝ ተናግረው፥ ቤተ ክርስቲያን ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን በማቅረብ፣ በማጽናናት እና ሀገሪቱን ወደ ጥልቅ ስቃይ የሚወደውን ጦርነት ለመቀልበስ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በማድረግ ላይ እንደምትገኝ ተናግረዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በየቀኑ ወደ 500 የሚጠጉ ሰዎች የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ከሶርያ እንደሚወጡ ይገምታል።

ከሶርያ ድንበሮች አልፎ የሚያስተጋባው የብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ ተማጽኖ ወደ ግጭት በተመለሰ ዓለም ውስጥ ተሰሚነትን ያላገኝ እንደሆነ ይነገራል። የሰላም፣ የመተሳሰብ እና የወንድማማችነት ዓለም መገንባት፥ የሰው ልጅ ክብር የፖለቲካ ጥረቶች ማዕከል የሆነበት ዓለም መገንባት የሚቻል ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ እንደሆነ ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ ተናግረዋል።

የዓለም ማኅበረሰብ ከሶርያ ሕዝብ ፊቱን ሊያዞር አይችልም ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ማሪዮ ዘናሪ፥ ስደተኞች በባሕር ውስጥ ሲሞቱ ደንታ ቢስ መሆን እንደማይቻል፥ አምባገነኖችን እና ጦርነቶችን መቀበል እንደማይችሉ እያንዳንዳችን በራሳችን የተፅዕኖ ፈጣሪነት፣ የውይይት መድረክ፣ የእርስ በርስ ግንኝነት እና የሰላም መንገዶችን እንድንገነባ ተጠርተናል ሲሉ በሶርያ የቅድስት መንበር እንደራሴ ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ ያለፈው እሑድ በመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተናግረዋል።

ካርዲናል ዘናሪ በመሬት መንቀጥቀጥ የተጎዱ በአሌፖ የሚገኙትን ጉዳተኞች ሲጎበኟቸው
ካርዲናል ዘናሪ በመሬት መንቀጥቀጥ የተጎዱ በአሌፖ የሚገኙትን ጉዳተኞች ሲጎበኟቸው

 

 

24 September 2024, 16:53