SAʴý

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ በቃለ ምልልሳቸው ወቅት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ በቃለ ምልልሳቸው ወቅት  (ANSA)

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓሊያ፥ ሰላምን መገንባት መንፈሳዊ መለወጥን እንደሚጠይቅ ገለጹ

በቫቲካን የሥነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ፕሬዝዳንት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ፥ በጣሊያን ሪሚኒ ከተማ ከነሐሴ 14-19/2016 ዓ. ም. የተካሄደውን 45ኛ የሕዝቦች የኅብረት እና የነጻነት ዓመታዊ ጉባኤን በማስመልከት ከቫቲካን መገናኛ ብዙኃን ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። ብጹዕ አቡነ ፓሊያ የክርስቲያኖችን የሰላም ገንቢነት ሚናን በማንፀባረቅ በጦርነት በሚሰቃይ ዓለም ውስጥ ሰላምን ለመገንባት መንፈሳዊ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“በጦርነት በሚሰቃይ ዓለም ውስጥ ሰላምን ለመገንባት የሚያስችል የወንድማማችነት ወንጌል እንደገና ማግኘት ያስፈልጋል የሚለው የቃለ ምልልሳቸው ዋና ጭብጥ እንደሆነ ታውቋል። የጳጳሳዊ የሕይወት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓሊያ ሐሙስ ነሐሴ 16/2016 ዓ. ም. ከጣሊያን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ አንቶኒዮ ታጃኒ ጋር “የሰላም ጎዳናዎች” በሚል ርዕሥ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ንግግር አድርገዋል።

ለብዙ ሰዎች ሰላም የሚለው ቃል እንደ ረቂቅ ቃል እንደሆነ የገለጹት ብጹዕ አቡነ ፓሊያ፥ ሰላምን ለመገንባት ተስፋ መቁረጥ እንደማይገባ አሳስበው፥ ዛሬ በጣሊያን እና በአውሮፓ ብቻ ሳይሆን በዓለም ውስጥ የጠፋው የሰላም ራዕይ እንደሆነ ገልጸው፥ እርስ በርስ መገናኘት በተቻለበት እና በኢኮኖሚው የበላይነት በተያዘ ዓለም ውስጥ ሁሉም ሰው የራሱን የግል ፍላጎት ወይም አጀንዳን በማስከበር እና በማስጠበቅ ላይ እንደሚያተኩር ሁሉ አገሮች እና ግለሰቦች ለራሳቸው ጉዳይ ብቻ ትኩረትን ሰጥተዋል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጋራ መኖሪያ ምድራችን እንደ አንድ ቤተሰብ መኖራችንን “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው በራዕይ መናገራቸውን ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ፓሊያ፥ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች በሙሉ የጋራ አባት እንዳለን ማመን ለሰላም ወሳኝ ነው ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አልፎ አልፎ የሚታዩት ጦርነቶች ብለው የሚጠሩትን የሦስተኛውን የዓለም ጦርነት እያሰብን እንፈራለን ያሉት ብጹዕ አቡነ ፓሊያ፥ እንደ እውነቱ ከሆነ እነዚህ ጦርነቶች የማይታሰብ አሳዛኝ ሁኔታዎችን እያስከተሉ እንደሆነ፣ ምንም እንኳን ባሁኑ ጊዜ በዓለማችን ውስጥ 59 ጦርነቶች በመካሄድ ላይ ቢሆኑም በዩክሬን እና በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ ስላሉ ሁለት ጦርነቶች ብቻ እንደሚነገር ገልጸው፥ ወሳኙ ነጥብ ሰላምን ማምጣት የሁሉ ሰው ሃላፊነት መሆኑን ለመረዳት መንፈሳዊ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ እና ይህን ብዙዎች እንደ ቀላል ቢመለከቱትም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተኩረት የያዙት የወንጌል ትንቢት እንደሆነ አስረድተዋል።

ብዙ ሰዎች በጦርነት አደጋ ውስጥ እንደሚገኙ የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓሊያ፥ “ሰዎች በቆራጥነት ከተነሱ ሰላምን መፍጠር እንደሚችሉ፥ በዩክሬን ስላለው ጦርነት ምን አገባን ወይም ምንም ማድረግ አንችልም” ማለት እንደማይችሉ ገልጸው፥ በሚሆነው ነገር ሊያዝኑ እና ሊቆጡ ብችሉም ነገር ግን በሌላ ወገን ለሰላም በመጸለይ አብሮነትን ከሚያራምዱ ቁርጠኛ ከሆኑ ብዙ ሰዎች ጋር መተባበር የሚችሉባቸው በርካታ ነገሮች እንዳሉ አስረድተዋል። “ከአጥፊው ግለሰባዊነት ወደ ወንድማማችነት መሸጋገር አለብን” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓሊያ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሚናገሩት ታላቅ ለውጥ ላይ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳትሆን ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ተሳታፊ እንደሚሆኑ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ብጹዕ ውቅዱሳን ፓትርያርክ አቴናጎረስ ከቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ ጋር ባደረጉት ታሪካዊ ግንኝነት ወቅት ባቀረቡት የሚያምር አገላለጽ፥ አብያተ ክርስቲያናት ቢከፋፈሉ እህት አብያተ ክርስቲያናት እና ወንድማማች ሕዝቦች ምን ይሆናሉ?” በማለት ያቀረቡትን ጥያቄ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓሊያ አስታውሰዋል።

ቅዱስ ወንጌል ሁሉም ነገር እንደሚቻል በግልጽ እንደሚነግረን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓሊያ፥ “እኛ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ረቂቅ ታሪክ ሳይሆን እንደ ኃይል ምንጭ አድርገን እንደገና ማግኘት አለብን፤ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነታውን የመቀየር ኃላፊነት አለብን፤ ደቀ መዛሙርቱም እንዲሁ እንዲያደርጉ ኃይልን ስለሰጣቸው እኛም በዚህ መስመር መቀጠል አለብን” ብለው፥ ውስጣዊ ውጥረት የታሪካዊ ለውጥ እውነታ እንዲሆን ወንጌልን በታላቅ ቅንነት በእውነት ተቀብለን በየቀኑ እንደገና ማንበብ መጀመር እንደያስፈልግ አሳስበዋል።

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ “የእርሱ ቤተ ክርስቲያን” በሚለው የመጀመሪያው ቃለ ምዕዳናቸው ላይ “አንድ ክርስቲያን በተፈጥሮው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ፣ ከክርስቲያኖች ጋር ባለው ግንኙነት፣ ከሌሎች ሃይማኖቶች እና ከማያምኑት ጋርም ቢሆን ዓለም አቀፋዊ ነው” ማለታቸውን የጠቀሱት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓሊያ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማንነታችንን መጠበቅ ግልጽነትን እንደሚጠይቅ እና ማንነታችንም ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነት መሆኑን ያሰመሩበት ለዚህም ነው” ብለው፥ የአሲሲው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ እና ቅዱስ ቻርለስ ደ ፎኩዎ የዚህ ምሳሌዎች በመሆናቸው ሁሉም ክርስቲያኖች ይህንን የእግዚአብሔርን ጥሪ እንዲለማመዱት መፈለጋቸውን ገልጸዋል።

እርስ በርስ መፋቀር እና መዋደድ ሰላምን ለመገንባት አስፈላጊ እንደሆኑ የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓሊያ፥
በቤተሰብ መካከል እና በቤት ውስጥ ሰላምን መገንባት አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው፥ ብዙውን ጊዜ ጦርነቶች ከቤት የሚጀምሩ በመሆናቸው ከዚህ አንጻር እርስ በርሳችን በመዋደድ እና አንዳችን ሌላውን የምንከባከብ ከሆነ ጦርነትን ማሸነፍ እንደሚቻል፥ በቫቲካን የሥነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ፕሬዝዳንት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ በቃለ ምልልሳቸው አስገንዝበዋል።

 

26 August 2024, 14:56