SAʴý

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጉባኤን በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አስጀመሩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንችስኮስ ከመስከረም 22 እስከ ጥቅምት 17/2017 ዓ. ም. የሚካሄደውን የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጉባኤን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በይፋ አስጀምረዋል።ቅዱስነታቸው መስከረም 22/2017 ዓ. ም. ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት፥ ሲኖዶሶዊ ጉዙ በኅብረት የሚደረግ እንደሆነ አስገንዝበው በጉባኤው ወቅት የሚደረግ አስተዋጽዖ በስጦታ የሚቀርብ እንጂ ጫናን የሚያደርግ እንዳልሆነ አስረድተዋል። ክቡራት እና ክቡራን፥ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሲኖዶስ መደበኛ ጉባኤ ሁለተኛ ምዕራፍን ምክንያት በማድረግ ባሳረጉት የመክፈቻ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያሰሙትን ስብከት ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጉባኤ ሁለተኛ ምዕራፍ በምንከፍትበት በዛሬው ዕለት የምናቀርበው መስዋዕተ ቅዳሴ ጠባቂዎቻችንን የሆኑ ቅዱሳን መላእክትን በማሰብ ነው። በዕለቱ የተነበበውን የእግዚአብሔርን ቃል ካዳመጥን በኋላ፣ ለግንዛቤችን መነሻ የሚሆኑ ሦስት ቃላትን እንውሰድ። እነርሱም፥ ድምፅ፣ መሸሸጊያ እና ሕጻን ናቸው።

‘ድምጽ’ ወደ ተስፋይቱ ምድር በሚወስደው መንገድ ላይ ሕዝቡ እግዚአብሔር የላከውን የመልአኩን ድምፅ እንዲያዳምጡ መከራቸው። (ዘፀ. 23፡20-22)። ይህ ምስል ከእኛ ጋር ተዛማጅነት ያለው ነው። ይህን ሲኖዶሳዊ ጉዞ በኅብረት በንጓዝበት ወቅት እግዚአብሔር የታላቅ ሕዝብ ታሪክ፣ ሕልማቸውን እና ተስፋቸውን ይሰጠናል። እነዚህ ታላቅ ሕዝቦች በዓለም ዙሪያ የተበተኑ እህቶቻችን እና ወንድሞቻችን፣ በአንድ እምነት የተነሳሱ እና ተመሳሳይ የቅድስና ፍላጎት ያላቸው ናቸው። ከእነርሱ ጋር እና ለእነርሱም ጭምር እግዚአብሔር ወደ ሚፈልገው መዳረሻ ለመድረስ መከተል ያለብን መንገድ የቱ እንደሆነ ለመረዳት እንትጋ። ነገር ግን የመልአኩን ድምፅ እንዴት መስማት እንችላለን?

ይህን ድምጽ መስማት የምንችልበት አንዱ መንገድ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ከዓለም ዙሪያ የተሰበሰቡትን የሕዝበ እግዚአብሔር ድምጾች በሙሉ በአክብሮት እና በትኩረት፣ በጸሎት እና በእግዚአብሔር ቃል በመቀበል ነው። እነዚህ ሦስት ዓመታት አእምሮአችንን እና ልቦቻችንን ለማንጻት የማያቋርጥ ጥረት በማድረግ ከባድ ሥራዎች የተከናወኑባቸው፥ ሃሳቦች የተጋሩባቸው እና ውይይቶች የተሄዱባቸው ናቸው። በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ እነዚህን ድምፆች ማዳመጥ እና መረዳት አለብን። ማለትም ከጉባኤው የሚፈልቁ ሃሳቦችን፣ ሕዝበ እግዚአብሔር የሚጠብቋቸው ውጤቶችን እና የሚቀርቡ የውሳኔ ሃሳቦችን፥ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን በሚናገረው ድምጽ ላይ በኅብረት ስናስተነትን ነው።

ደጋግመን እንደገለጽነው ይህ ጉባኤ የፓርላማ ጉባኤ ሳይሆን፥ ታላቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ በብከቱ፥ ‘አንድ ሰው በልቡ የያዘውን ወይም አንዲት ሴት በልቧ በከፊል የያዘችውን ወይም ሌላው በሙላት የያዘውን እና አንዳንዶች የተለያዩ ስጦታዎች ቢኖሯቸውም በመንፈስ ቅዱስ ልግስና ሁሉም ነገር የሁሉም ነው’ እንዳለው፥ ከመላው የእግዚአብሔር ሕዝብ እና ከጉባኤው ተካፋዮች የሚቀርቡ ድምጾችን በኅብረት የምናዳምጥበት ቦታ ነው።

ነገር ግን ይህ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ አንድ ቅድመ ሁኔታ ተቀምጧል። በብዝሃነታችን መካከል አንድነት እና ስምምነት የሚሰጠውን የመንፈስ ቅዱስ ቸርነት በውስጣችን እንዳይኖር ከሚከለክሉ ነገሮች ራሳችንን ነጻ ማድረግ አለብን። በትዕቢት ተነሳስተው የእግዚአብሔርን ድምፅ የመስማት ልዩ መብት አለን የሚሉ ሊሰሙት አይችሉም (ማር. 9፡38-39)። በምስጋና እና በትኅትና የምንቀበለው እያንዳንዱን ቃል ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችን ጥቅም ሲል እግዚአብሔር የሚሰጠን በመሆኑ ማስተጋባት ይችላል (ማቴ. 10፡7-8)።

ከመካከላችን የሚቀርቡ ሃሳቦችን በግድ ለመጫን እንደሚቀርቡ አድርጎ ከመውሰድ እንጠንቀቅ። የራሳችንን አመለካከት እንኳን ወደ ጎን በመተው ሕይወት ያለውን አዲስ ነገር ለማግኘት ሲባል እያንዳንዳችን በስጦታነት የምናቀርባቸውን ሃሳቦች ከሌሎች ጋር ለመጋራት ዝግጁዎች እንደሆናችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። ያለበለዚያ የጉባኤው ተሳታፊዎች የሌሎችን ሃሳብ፥ ከሁሉም በላይ ደግሞ የእግዚአብሔርን ድምፅ ሳንሰማ የራሳችንን ዓላማ ወይም አጀንዳ ብቻ ለማራመድ በምንፈልግበት እና መደማመጥ በማንችልበት ውይይት ውስጥ ልንገባ እንችላለን።

ለሚያጋጥሙን ችግሮች እኛ መፍትሄ የለንም። መፍትሄ ያለው በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ነው። (ዮሐ. 14፡6)። በረሃ ውስጥ ሆናችሁ ትኩረትን ማጣት እንደማትችሉ አስታውሱ። ለሚሰጥ መመሪያው ትኩረት የማትሰጡ ከሆነ ወይም ብቻችሁን ልትወጡት የምትችሉ መስሎ ከታያችሁ በረሃብ ወይም በጥማት ልትሞቱ ትችላላችሁ። ከእናንተም ጋር አብሮአችሁ ያሉት ሰዎች ሊሞቱባችሁ ይችላሉ። እንግዲያውስ ከውስንነታችን እና ከችግራችን ጋር መንገዳችንን በሰላም ለመጓዝ የእግዚአብሔርን እና የመልአኩን ድምፅ እንስማ (መዝ. 23፡4)።

ይህ ‘መሸሸጊያ’ ወደሚለው ቀጣዩ ቃል ይወስደናል። መሸሸጊያ የሚለው ቃል እኛን ከአደጋ ሊጠብቁን በሚችሉ ክንፎች ሊገለጽ ይችላል። ‘በላባዎቹ ይጋርድሃል፤ ከክንፎቹም በታች ትጠለላለህ፥ ታማኝነቱ እንደ ጋሻ እና እንደ ቅጥር ይከብብሃል’ (መዝ 91: 4)። ክንፎች በጠንካራ እንቅስቃሴ አካልን ከመሬት ላይ ማንሳት የሚችሉ ኃይለኛ መሣሪያዎች ናቸው። ክንፎች ምንም እንኳን ጥንካሬን ቢወክሉም አንድ ላይ ሰብሰብ አድርጎ ለመያዝ፣ ሙቀት እና ጥበቃ ለሚያስፈልጋቸው ጫጩቶች ጋሻ እና መጠለያ ጎጆ ይሆናሉ።

ይህ እግዚአብሔር ለእኛ የሚያደርግልን ነገር ምልክት ነው። በተለይ በዚህ ዘመን ስንሰበሰብ ልንከተለው የሚገባን አርአያ ነው። በመካከላችን ብዙ ወንድሞች እና እህቶች በጠንካራ የአስተሳሰብ ችሎታቸው እና በብሩህ ግንዛቤያቸው ወደ ከፍታ ሥፍራ የመውጣት ብቃት ያላቸው እና በሚገባ የተዘጋጁ አሉ። ይህ ሁሉ ለኛ ትልቅ ጥቅም ነው። ያነሳሳናል፣ ይፈትሸናል፤ አንዳንዴም በግልፅ እንድናስብ እና በቆራጥነት ወደ ፊት እንድንጓዝ ያስገድደናል። ፈተናዎች እና ችግሮች ቢያጋጥሙንም በእምነት ጸንተን እንድንኖርም ይረዳናል። ይህ ስጦታችን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ጉልበቶቻችንን ለማዝናናት እና ዝቅ ብለን እርስ በርስ የመቀባበል፣ የመተቃቀፍ እና መሸሸጊያ ቦታን ለማቅረብ የሚያስችለን መሆን አለበት። በዚህ መንገድ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ግንቦት 9/1974 ዓ. ም. ለጣሊያን ፕሬዚዳንታዊ ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ‘የወንድሞች እና የእህቶች ቤት፣ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያለው አውደ ጥናት እና የጠንካራ መንፈሳዊነት ማማ ነው’ ማለታቸው ይታወሳል።

በዙሪያችን የሚወዱን፣ የሚያከብሩን እና የሚያደንቁን፣ የምንናገረውን ለማዳመጥ የሚፈልጉ ወዳጆች መኖራቸውን በተገነዘብን መጠን ራሳችንን በግልፅ ለመግለጽ ነፃነት ይሰማናል። ይህ የውይይት እና የጋራ ግንኙነት ሁኔታዎችን የማመቻቸት ዘዴ ብቻ አይደለም። ማቀፍ፣ ከአደጋ መጠበቅ እና መንከባከብ በእውነቱ የቤተ ክርስቲያን ተፈጥሮ አካል ነው። ቤተ ክርስቲያን በተጠራችበት ጥሪ፥ ቸርነት በሚጠይቀው ፍጹም ስምምነት ወደ ሥነ-ምግባራዊ ጥንካሬ፣ ወደ መንፈሳዊ ውበት እና ተስማሚ ቦታ የሚመራ የመሰብሰቢያ ቦታ ነው። እያንዳንዱ ሰው በእናቱ እቅፍ ውስጥ እንዳለ ሕጻን (ኢሳ. 49፡15፤ 66፡13) እና እስከ አባቱ ጉንጭ ድረስ ከፍ የተደረገ ሕጻን የሚሰማው ስሜት እና ቤተ ክርስቲያን ከሁሉም በላይ ልባችን ውስጥ ሰላም እና ቦታ ሊኖራት ያስፈልጋል። (ሆሴዕ 11:4፣ መዝ. 103:13)

ሦስተኛው ቃል ‘ሕጻን’ ወደሚለው ይወስደናል። በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ሕፃንን በደቀ መዛሙርቱ መካከል ማስቀመጡን እና ደቀ መዛሙርቱ ሕጻኑን አይተው እንዲለወጡ እና እንደ እርሱ ትንሽ እንዲሆኑ መጋበዙን ያስታውሰናል። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን “በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው?” ብለው በጠየቁት ጊዜ እርሱም ‘እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ ወደ መንግሥተ ሰማይ ከቶ አትገቡም” በማለት ሕጻናትን እንዲመስሉ በማበረታታት መለሰላቸው። ነገር ግን ይህ ብቻ አይደለም። “እንደዚህ ሕጻን ያለውን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል’ (ማቴ. 18፡1-5) በማለት አክሎ ተናግሯል ።

ይህ ምሳሌ ለኛ እጅግ አስፈላጊ ነው። የሲኖዶሱን አስፈላጊነት ስንመለከት በተወሰነ መልኩ በመንፈስ፣ በልባችን፣ በአመለካከታችን ታላቅ ለመሆን መጣር አለብን። ምክንያቱም ልንመለከታቸው የሚገቡን ጉዳዮች ታላቅ እና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያሻቸው ስለሆኑ ሁኔታዎችም ሰፊ እና ሁሉን አቀፍ ናቸው። በስብሰባዎቻችን እና በውይይት ገበታዎቻችን መሃል ኢየሱስ ክርስቶስ በደቀ መዛሙርቱ መካከል ያስቀመጠውን ሕፃን ማየት መዘንጋት የለብንም። ኢየሱስ ይህን ያደረገው ለተሰጠን ኃላፊነት ብቁ ለመሆን የሚቻለው ራሳችንን ትንሽ አድርገን በትሕትና እርስ በርስ መቀባበል እንደሚገባ ለማስገንዘብ ነው።

‘እግዚአብሔር ራሱን ትንሽ በማድረግ እውነተኛ ታላቅነት ምን ማለት እንደሆነ፣ በእውነትም አምላክ መሆን ምን ማለት እንደሆነ አሳይቶናል’ (ር. ሊ. ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛ እ.አ.አ. ጥር 11/2009)። ኢየሱስ፥ ‘የልጆች መላእክት ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ’ (ማቴ 18:10) ያለው በአጋጣሚ አይደለም። በሌላ አነጋገር ሕጻናት የአብን ፍቅር በቅርበት እንደሚያሳይ መነጽር ናቸው።

እንግዲያውስ በዚህ መስዋዕተ ቅዳሴ ወደፊት የሚመጡትን ቀናት በመደማመጥ፣ በመተሳሰብ እና በትህትና መንፈስ ለመኖር እንዲረዳን ጌታን እንለምነው። የመንፈስ ቅዱስን ድምጽ እናዳምጥ፤ በፍቅር እንደተቀበልን እየተሰማን፣ የታመነውን፣ ንጹሐን እና ቀላል የሆኑ የሕጻናት ዓይን ይኑረን። እኛ ድምጻቸው እንሁን፤ ምክንያቱም በእነርሱ በኩል ጌታ ነፃነታችንን በአግባቡ እንድንጠቀም እና የመለወጥን አስፈላጊነት እንድናስታውስ መጥራቱን ይቀጥላል።”

 

02 October 2024, 17:33