SAʴý

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ተመጣጣኝ ያልሆነ ራስን መከላከል በሙሉ ሥነ-ምግባር የጎደለው ነው”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሁለት የአውሮፓ አገራት ሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም ያደረጉትን 46ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ፈጽመው ሲመለሱ በረራ ላይ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ልዩ ልዩ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። ቅዱስነታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት ምላሽ፥ በሊባኖስ ሃሰን ናስራላህን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ አውግዘዋል። በተጨማሪም ውርጃን ሕጋዊ ከማድረግ ይልቅ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ የመረጡትን ንጉሥ ባውዶይንን ለክርስቲያናዊ ምስክርነታቸው አወድሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው እሑዱ መስከረም 19/2017 ዓ. ም. ወደ ሮም በመመለስ ላይ እያሉ መግለጫ ሰጥተዋል። የቅድስት መንበር የመግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዮ ብሩኒ አብረዋቸው የተጓዙት ጋዜጠኞች ጥያቄዎቻቸውን ከማቅረባቸው በፊት ቅዱስነታቸውን አቅርበዋል።

ቅዱስነታቸውም በበኩላቸው አብረዋቸው የተጓዙት በሙሉ ካመሰገኑ በኋላ በሰጡት ምላሽ፥ ሉክሰምበርግ ሚዛናዊ ማኅበረሰብ፣ በሚገባ ታስበው የጸደቁ ሕጎች እና ባሕል ያላት አገር በመሆኗ አድናቆታቸውን ገልጸዋል። በሌላ በኩል ቤልጂየምን በሚገባ እንደሚያቋት የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ ሉክሰምበርግን ለሚዛናዊነቷ እና ለመስተንግዶዋ አድንቀው ምናልባትም ለአውሮፓ አኅጉር ልታቀርብ የምትችለው መልዕክትም ይህ እንደሆነ ገልጸዋል።

አንዳንዶች በቤልጂየም ዲሞክራሲያዊ ሂደት ላይ እንደተደረገ ፖለቲካዊ ጣልቃገብነት ቢመለከቱትም የንጉሡን የብጽዕና አዋጅ ሂደት ከሥልጣን ጋር ማያያዝን፥ እንዲሁም በሕይወት የመኖር መብትን ለሴቶች ከሚሰጥ የሕይወት ጥበቃን በማስታወስ እንደተናገሩት፥ ጉዳዩ ታላቅ ክብር የሚሰውን የሰውን ሕይወት የሚመለከት መሆኑን ገልጸው፥ ንጉሥ ባውዶይን በድፍረት በመነሳት ሞትን የሚደግፍ ሕግ ለማጽደቅ አለመፈለጋቸው አስታውሰው “ይህን ለማድረግ እውነተኛ ፖለቲከኛ መሆን ያስፈልጋል” ብለዋል።

“ሴቶች በሕይወት የመኖር መብት አላቸው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ውርጃን ማካሄድ ነፍስ መግደል መሆኑን ማስተዋል እንደሚገባ እና በእናት ማሕጸን ውስጥ ጽንስ በአንድ ወር ውስጥ ሁሉም የሰውነት ክፍሎች በግልጽ እንደሚታዩ ሳይንስ እንደሚያስረዳ ተናግረዋል። በዚህ ደረጃ ላይ ያለን ጽንስ ዕድገቱን ማቋረጥ ነፍስ ማጥፋት መሆኑ ሊያከራከር እንደማይችል እና ሴቶች ይህን ሕይወት ከሞት አደጋ የመጠበቅ መብት እንዳላቸው አስረድተዋል።

በብራስልስ ውስጥ በሕጻናት ላይ የተፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃቶችን በማስመልከት የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በተመለከተ እና በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ያስከተለውን አደጋ በተሻለ መንገድ በመፍታት የምእመናንን አመኔታ መልሶ ማግኘትን በማስመልከት እንደተናገሩት፥ ጉዳዩን ተከታትሎ እልባት የሚሰጥ አንድ መምሪያ በቫቲካን ውስጥ መቋቋሙን እና በኮሎምቢያዊው ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ኦሜሌ ፕሬዚደንትንት የሚመራ መሆኑን አስረድተዋል።

ቅዱስነታቸው በማከልም በዚህ ርዕሥ ዙሪያ የሚነሱ ነጥቦች በሙሉ በቫቲካን ውይይት እንደሚደረግባቸው እና በደል የደረሰባቸውን ሰዎች በቫቲካን ተቀብለው ማጽናናታቸውን አስታውሰዋል። እነዚህን ሰዎች ቀርቦ ማዳመጥ ግዴታ መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከ 40-42-46% ወሲባዊ ጥቃት የሚፈጸመው በቤተሰብ እና በሠፈር ውስጥ እንደሆነ ጠቅሰው፥ ጥቃቱ በቤተ ክርስቲያን የሚፈጸምባቸው 3% ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል።

“ጥቃት የደረሰባቸውን ሰዎች የመርዳት እና የመንከባከብ ሃላፊነት አለብን” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ አንዳንዶቹ የሥነ ልቦና ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው እና በዚህም መንገድ መርዳት እንደሚገባ ተናግረው፥ የካሳ ክፍያም በማስመልከት እንደተናገሩትም እርግጠኛ ባይሆኑም በቤልጂየም ሕግ መሠረት የካሣ ክፍያው መጠን 50,000 ዩሮ እንደሆነ እና ይህም ዝቅተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።


ጥቃት የተፈጸመባቸውን መንከባከብ እና ጥቃት የፈጸመውንም በሕግ መቅጣት እንደሚገባ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ይህ በደል የዘመናችን ብቻ ባይሆንም ምናልባት ነገ ላይከሰት ይችላል ብለዋል። ሥነ ልቦናዊ ሕመም የሚያስከትል በመሆኑ ለተጠቂዎቹ ሕክምና እና ክትትል ሊደረግላቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።

አጥፊው በነጻነት መደበኛ ኑሮን እንዲኖር በማድረግ በቁምስናዎች እና በትምህርት ቤቶች ውስጥ በሃላፊነት ማስቀመጥ እንደማይቻል ተናግረው፥ አንዳንድ ጳጳሳት ጥፋት ለፈጸሙት ካህናት የሥራ ዕድል ቢሰጡም ነገር ግን ሕፃናት በሚገኙበት ቦታ መሆን እንደሌለበት በማሳሰብ፥ ድርጊቱ አሳፋሪ ቢሆንም የቤልጂየም ብጹዓን ጳጳሳት ተስፋን ሳይቆርጡ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ ማበረታታቸውን ገልጸዋል።

የጋዛን ምዕመናን በየዕለቱ እንደሚያሳታውሷቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ ከ600 በላይ ሰዎች በካቶሊካዊ ቁምስና እና ትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ እና እየተፈጸሙ ያሉ ጭካኔዎችን ጨምሮ የአካባቢው ጠቅላላ ሁኔታ በየዕለቱ እንደሚነገራቸው ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር ተመጣጣኝ ያልሆነ ራስን መከላከል በሙሉ ሥነ-ምግባር የጎደለው እንደሆነ ገልጸዋል። አንድን አገር ብቻ ሳይሆን ኃይልን የሚጠቀም ማንኛውም አገር ይህን የመሰለ ነገር ቢሠራ ድርጊቱም ኢ-ሞራላዊ ነው በማለት አስረድተዋል።

ሴቶችን በተመለከተ፥ ስለ ሴቶች ክብር ዘወትር እንደሚናገሩ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በዚህ አውድ ውስጥ የሚናገሩት ስለ ወንዶች ሳይሆን ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን የእናትነት መጠሪያ እና የኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽራ እንደሆነች አስታውሰዋል። ቤተ ክርስቲያንን ተባዕታይ በማድረግ ሴቶችን በወንድነት መጥራት ሰብዓዊነት እና ክርስቲያናዊ እንዳልሆነ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ ሴትነት የራሱ ጥንካሬ እንዳለው እና እንደውም ሴቶች ከወንዶች የበለጠ አስፈላጊ እንደሆኑ፣ ቤተ ክርስቲያን ሴት እና የኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽራ እንደሆነች አስረድተዋል።

“ሴት ከወንድ ጋር እኩል ነች!?” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ሴት እንደምትበልጥ እና ቤተ ክርስቲያን አንስታይ እንደሆነች፥ አገልግሎትን በተመለከተ የሴት ምሥጢራዊነት ከአገልግሎት እንደሚበልጥ አስረድተዋል። ይህን በሰፊው ያጠና አንድ ታላቅ የነገረ መለኮት ምሁር መኖሩን ገልጸው፥ የቅዱስ ጴጥሮስ አገልግሎት ወይስ የማርያም አገልግሎት ይበልጣል? ብሎ መጠየቁንም አስታውሰዋል። የማርያም አገልግሎት ሌሎችን የሚያካትት የአንድነት አገልግሎት እንደሆነ እና ነገር ግን የቅዱስ አገጅልግሎት የአስተዳደር አገልግሎት መሆኑን አስረድተዋል።

“የቤተ ክርስቲያን እናትነት የሴት የእናትነት ተፈጥሮ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ አገልግሎት ምንጊዜም በእናትነት ተፈጥሮ ውስጥ ከምእመናን ጋር ለመጓዝ የታለመ አገልግሎት መሆኑን አስረድተው፥ የተለያዩ የነገረ-መለኮት ሊቃውንት ይህን ከዘመናት በፊት ቢያጠኑትም ጊዜ ያለፈበት ሳይሆን ዛሬም እውነት እንደሆነ ተናግረዋል።

ቅዱስነታቸው ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች እና በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት አብረዋቸው የነበሩት ላበረከቱት ሥራ ምስጋናቸውን አቅርበው፥ በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው እንዲሁም እነርሱም እንዲጸልዩላቸው አደራ ብለዋል።

በካናሪ ደሴቶች የባሕር ዳርቻ ሕይወታቸውን ያጡ የሃምሳ ሰዎች አሳዛኝ ሁኔታን በማስታወስ የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው፥ ነፃነት ፍለጋ ወጥተው በባሕር ላይ ሕይወታቸውን ያጡ በርካታ ስደተኞች መኖራቸውን በማስታወስ የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸዋል።


 

01 October 2024, 09:14