SAʴý

የሜዲቴራኒያን ባሕር በጀልባ ለማቋረት የሚሞክሩ ስደተኞች የሜዲቴራኒያን ባሕር በጀልባ ለማቋረት የሚሞክሩ ስደተኞች  (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ወንድማማችነት ለግዴለሽነት ባሕል መልስ ሊሆን እንደሚችል ተናገሩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከመስከረም 5-11/2017 ዓ. ም. ድረስ በአልባኒያ ዋና ከተማ ቲራና እየተካሄደ ያለው ስብሰባ ተሳታፊዎች የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው፥ ሜዲትራኒያን ባሕር መቃብር መሆኑ ቀርቶ የወንድማማችነት እና የሰላም ባሕር ለማድረግ የተስፋ ተጓዦች በመሆን የእግዚአብሔርን ምልክቶች እንዲከተሉ ጋብዘዋቸዋል። “እያንዳንዱ ሰው የተቀደሰ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ስደተኞችን ለመቀበል እና የወዳጅነት በርን ለመክፈት የፍርሃት ባህልን መካድ አለብን ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በቪዲዮ መልክታቸው ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመማር የማይታክቱ የተስፋ ምዕመናን እና የእግዚአብሔርን ምልክቶች በመከተል የሜዲትራኒያን ባሕር የመቃብር ሥፍራ መሆኑ ቀርቶ እጅግ ውብ የወንድማማችነት እና የሰላም ገጽታን ያገኝ ዘንድ አደራ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከመስከረም 5-11/ 2017 ዓ. ም. በአልባኒያ መዲና ቲራና በመካሄድ ላይ ባለው የ “Med24” የመንፈሳዊ ጉዞ እና የተስፋ ስብሰባ ላይ ለተገኙት 25 የ “ማሬ ኖስትረም” እና ከጥቁር ባሕር ለተውጣጡ 50 ወጣቶች ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፥ “በሜዲትራኒያን አካባቢ በሚገኙ አገራት አብያተ ክርስቲያናት በመታገዝ የምንገነባው ሰላም እና ወንድማማችነት ለግጭቶች እና ለግድየለሽነት ልንሰጥ የምንችለው ከሁሉ የተሻለ ምላሽ ነው” ብለዋል። "

ወጣቶች የሜዲትራኒያን አካባቢ የወደፊት ዕጣ ናቸው
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከአሥር ዓመት በፊት ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መስከረም 21/2014 ወደ አልባኒያ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉዞ በማስታወስ፥ “የአገሪቱ ሕዝብ ብዙ መልክ ቢኖረውም በድፍረት የተዋሃደ ነው” በማለት ገልጸዋል።

ያኔ ለወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክት፥ “እናንተ የአልባኒያ አዲሱ ትውልድ ናችሁ። ከአምስቱ የሜዲትራኒያን የባሕር ዳርቻዎች መካከል የተከበራችሁ እና የሜዲትራኒያን አካባቢ የወደፊት ዕጣ ፈንታን የምትወስኑ አዲሱ ትውልድ ናችሁ” ማለታቸውንም አስታውሰዋል።

ሰላም ይገነባል፤ ግዴለሽነት ይገድላል
“ሁላችንም የተስፋ ነጋዲያን ነን” ሲሉ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በመቀጠልም፥ “እውነትን እየፈልግን፣ እምነታችንን እየኖርን እና ሰላምን እየገነባን እንገኛለን” ብለው፥ እግዚአብሔር በሰዎች መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት ሳያደርግ ሁሉንም ይወዳል” ሲሉ አስረድተው፥ “እየገነባችኋቸው ያላችሁት አምስቱ የሜዲትራኒያን የባሕር ዳርቻዎች ወንድማማችነት ሕይወትን በከንቱ ለሚያጠፉ ግጭቶች እና ግዴለሽነቶች በቂ ምላሾች ናቸው” ብለዋል።

እያንዳንዱ ሰው የተቀደሰ ነው፤ በክብር ተቀበሉት
“የባሕላችሁ ብዝሃነት ከእግዚአብሔር የተሰጥ ባለ ጠግነት መሆኑን አስታውሱ” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የባሕል እና የሃይማኖት ልዩነቶች የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው፤ በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነት የጋራ ክብራችን ነው” ብለዋል።

“ድምጻቸው የታፈነባቸውን ሰዎች ወደ ፊት አምጧቸው፤ እንደ ሸክም የሚቆጠሩ ድሆችን፣ በችግር ምክንያት የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ከገዛ አገራቸው የሚሰደዱ ወጣቶችን ተቀብላችሁ ተንከባበቧቸው” በማለት አክለዋል።
“የምናወራው ስለ ቁጥሮች ሳይሆን ስለ ሰዎች ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ እያንዳንዱ ሰው የተቀደሰ በመሆኑ ክብራቸው ማደግ እና መጠበቅ አለበት ብለው፥ የፍርሃት ባህልን በማስወገድ ስደተኞችን ለመቀብል የወዳጅነት በር ልንከፍት ይገባል ብለዋል።

የሜዲትራኒያን ባሕር የሚለማ ውብ የአትክልት ሥፍራ ይሁን!
“የሜዲትራኒያን ባሕር አንድ ያደርጋችኋል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እንደ ጥብርያዶስ ታላቅ ሐይቅ አደራን በመስጠት ለመታረስ እንደተዘጋጀ ውብ የአትክልት ቦታ አድርጋችሁ ኑሩበት” ብለዋል።“በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ ባለው የአገልግሎት መንፈስ እና በእጃችሁ ያለውን ፍጥረት እንድትንከባከቡት እና እንድትጠብቁት” በማለት ግብዣቸውን አቅርበዋል። የሜዲቴራኒያን አካባቢ አገሮች ሰማዕታት የሰጡትን ምስክርነት አስታውሱ፤ ድፍረታቸው የሃያ ሁለት ዓመቷ ብፁዕት ማሪያ ቱቺ እንዳደረገችው፥ ሰብዓዊነታችሁን የሚያበላሹ ሁከቶችን ሁሉ ለመቋቋም ያላችሁትን ቁርጠኝነት ሊያነሳሳ ይችላል” ብለዋል።

ከእንግዲህ የወንድማማችነት እና የሰላም ባሕር እንጂ የመቃብር ሥፍራ አይደለም!
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክታቸውን ሲደመድሙ፥ የአልባኒያ ሕዝብ የበላይ ጠባቂ እና የመልካም ምክር እናት ለሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአደራ በመስጠት፥ ወጣቶቹ ከንጹህ ልቧ እንዲማሩ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የተስፋ ተጓዦች እንዲሆኑ እና የእግዚአብሔርን ምልክቶች እንዲከተሉ በማሳሰብ፥ የሜዲቴራኒያን ባሕር እጅግ ውብ ወደሆነ የወንድማማችነት እና የሰላም ሥፍራነት የሚመለስ እንጂ የመቃብር ሥፍራ ሊሆን አይገባም ብለዋል።

 

18 September 2024, 17:10