SAʴý

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ አገልግሎት፣ ተልዕኮ እና ደስታ ዋና የወንጌል ተግባራት እንደሆኑ ገለጹ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ መስከረም 16/2017 ዓ. ም. በሉክሰምበርግ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ከአገሪቱ ካቶሊካዊ ምዕመና ጋር ተገናኝተው ንግግር አድርገዋል። ቅዱስነታቸው ለካቶሊክ ማኅበረሰብ ባደረጉት ንግግር ለአገልግሎት፣ ለተልዕኮ እና ለደስታ አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተው፥ ቤተ ክርስቲያን ሌሎችን ተቀብላ በማስተናገድ፣ በሚስዮናዊነት አገልግሎት እንድትሳተፍ እና ወንጌልን በደስታ ልብ በተጨባች እንድትኖረው በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሉክሰምበርግ እና በቤልጂየም በሚያደርጉት 46ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የመጀመሪያ አገር በሆነች ሉክሰምበርግ ውስጥ ለካቶሊክ ማኅበረሰብ ንግግር አድርገዋል። በሉክሰምበርግ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ከማርያማዊ የኢዮቤልዩ ነጋዲያን ጋር የተገናኘ ሲሆን፥ ይህም መንፈሳዊ ንግደት ለአራት መቶ ዓመታት የዘለቀ እና ለችግረኞች አፅናኝ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሚሰጠውን አክብሮት የሚገልጽ እንደሆነ ታውቋል። በሉክሰምበርግ ኖትር-ዳም ካቴድራል ለተሰበሰቡ ምእመናን በሦስት ቁልፍ መሪ ሃሳቦች ላይ እነርሱም አገልግሎት፣ ተልእኮ እና ደስታ በሚሉት ላይ በማትኮር ንግግር አድርገዋል።

ለአገልግሎት የተጠራች ቤተ ክርስቲያን
“ማገልገል” በሚለው የመጀመሪያ ነጥብ ላይ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ አገልግሎት ዋና የወንጌል ተግባር እንደሆነ ገልጸው፥ እንግዳ ተቀባይነት አንገብጋቢ የበጎ አድራጎት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ፍትሃዊም ጭምር እንደሆነ አስርድተው፥ የሉክሰምበርግ ምእመናን ግልጽነትን በማድነቅ በዚህ ተግባራቸው ጸንተው እንዲቆዩ በማሳሰብ “የወንጌል ዋና ተግባር ማንንም ሳያገልሉ ሁሉንም በግልጽነት እና በእንግድነት ተቀብሎ ማገልገል ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሉክሰምበርግ ከካቶሊክ ማኅበረሰብ ጋር በተገናኙበት ወቅት
ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሉክሰምበርግ ከካቶሊክ ማኅበረሰብ ጋር በተገናኙበት ወቅት

ቤተ ክርስቲያን በዓለማዊ ማኅበረሰብ ውስጥ!
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ተልዕኮ” በሚለው የንግግራቸው ሁለተኛ ነጥብ ላይ በማትኮር፥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው ዓለማዊነት ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ሚና ምን መሆን እንደሚገባ በማስታወስ፥ ቤተ ክርስቲያን ለዋና እሴቶቿ ያላትን ዕይታ ማጣት እንደሌለባት አደራ ብለዋል። ቅዱስነታቸው ለሉክሰምበርግ ካቶሊክ ምዕመናን በለገሡት ምክር፥ አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅ ለዘመኑ ተግዳሮቶች ሁል ጊዜ ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቀው፥ በሐዘን፣ በተስፋ መቁረጥ ወይም በቁጭት እራሳችንን መት አንችልም” ብለው፥ ይህ ተፈጻሚ የሚሆነው ተልዕኮ ያላት ቤተ ክርስቲያን አካል ስንሆን ነው” ብለዋል።

የሉክሰምበርግ ካቶሊክ ምዕመናንም ይህንን በልባቸው ይዘው የማኅበረሰቡን ሕይወት ለማጠናከር እና የወንጌል መልዕክት ለማሰራጨት የሲኖዶሳዊነት መንፈስ እንዲከተሉ አደራ ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሉክሰምቡርግ ለካቶሊክ ማኅበረሰብ ንግግር ሲያደርጉ
ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሉክሰምቡርግ ለካቶሊክ ማኅበረሰብ ንግግር ሲያደርጉ

የወንጌል ደስታ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ደስታ” የሚለውን ሦስተኛውን የንግግራቸውን ጭብጥ በማስታወስ፥ ደስታ የክርስትና እምነት ዋና አካል እንደሆነ ገልጸዋል። ዲዮጎ የተባለ አንድ ወጣት በዓለም የወጣቶች ቀን ባካፈለው የደስታ ልምድ ምስክርነት ላይ በማሰላሰል፥ “እምነታችን በደስታ የተሞላ ነው፤ ምክንያቱም እኛ የእግዚአብሔር ተወዳጅ ልጆች መሆናችንን እናውቃለን” ያለውን በመጥቀስ፥ የወጣቱ የደስታ ምስክርነት የወንጌል መልዕክት ምሳሌ እንደሆነ አስረድተዋል።

ቅዱስነታቸው በፀደይ ወቅት በሉክሰምበርግ የሚደረገውን ልዩ መንፈሳዊ ጉዞን በማስታወስ፥ የቅዱስ ዊሊብሮርድን የሚስዮናዊነት ጥረት በሚያከብሩበት ወቅት ምእመናን በየጎዳናዎች የሚያሰሙት የደስታ ዝማሬዎች ትልቅ የአንድነት እና የደስታ መግለጫዎች ናቸው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸው ሲያጠቃልሉ፥ ምእመናን በአደራ የተሰጣቸው ተልዕኮ ውብ መሆኑን እንዲገነዘቡት አሳስበዋል።

 

27 September 2024, 17:07