SAʴý

በማያናማር ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎች ታይፎን ያጊ የሚባለው አውሎንፋስ ካስከተለው ከባድ የጎርፍ አደጋ በኋላ ውሃ ውስጥ ለመጓዝ ጊዜያዊ የቀርከሃ መንሳፈፊያዎችን ሲጠቀሙ  በማያናማር ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎች ታይፎን ያጊ የሚባለው አውሎንፋስ ካስከተለው ከባድ የጎርፍ አደጋ በኋላ ውሃ ውስጥ ለመጓዝ ጊዜያዊ የቀርከሃ መንሳፈፊያዎችን ሲጠቀሙ  

ብፁዕ ካርዲናል ቦ በማይናማር የጎርፍ አደጋ ከደረሰ በኋላ ዘላቂ የሆነ የመቋቋም አቅም እንዲገነባ ጠየቁ

የያንጎኑ ብጹእ ካርዲናል ቻርለስ ማውንግ ቦ በመሬት ላይ ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ እና እየተካሄደ ስላለው የእርዳታ ጥረቶች፣ በማናማር ውስጥ ያሉ በርካታ ግዛቶችን እና ክልሎችን ስላወደመው ከባድ የጎርፍ አደጋ እና የመሬት መንሸራተት አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ብፁዕ ካርዲናል ቻርለስ ሙአንግ ቦ ለሊካስ ዜና እንደተናገሩት ሁኔታው በእውነት ከባድ መሆኑን፣ ከጳጉሜ 4 ጀምሮ የጣለው ከባድ ዝናብ እና ታይፎን ያጊ ተብሎ የተሰየመው አውሎንፋስ በማዕከላዊ ማይናማር ላይ ከባድ የጎርፍ መጥለቅለቅን ማስከተሉን ጠቅሰው፥ በአደጋው በጣም የተጠቁ አካባቢዎች ማንዳላይ፣ ደቡባዊ ሻን፣ ምስራቃዊ ባጎ፣ ኬይን ግዛት እና ናይ ፒዪ ታው መሆናቸውን ገልጸዋል።

የያንጎኑ ሊቀ ጳጳስ እንዳሉት በሃገሪቷ በተከሰተው የእርስ በርስ ግጭት የተፈናቀሉትን ጨምሮ 887,000 የሚገመቱ ሰዎች በ65 የሃገሪቷ ከተሞች ውስጥ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸው፥ “በመሰረተ ልማቶች፣ በንብረቶች እና በህዝባዊ አገልግሎቶች ላይ የደረሰው ጉዳት አስከፊ ነው” ብለዋል።

ብጹእ ካርዲናል ቦ ተግዳሮቶቹ ብዙ መሆናቸውን ካብራሩ በኋላ የጎርፉ ውሃ በአብዛኛዎቹ ክልሎች መቀነሱን፣ ነገር ግን በአደጋው በጣም የተጎዱት አካባቢዎች እንደወደሙ፣ በመኖሪያ ቤቶች፣ በውሃ ምንጮች እና በመሠረተ ልማት ላይ ሰፊ ውድመት መድረሱን ጠቁመዋል።

በተደራሽ ንፁህ ውሃ እጦት ምክንያት የጤና ችግሮች እየተበራከቱ እንደሚገኙ እና ራቅ ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ የአደጋው ተጎጂዎች የምግብ፣ የመድኃኒትና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ለማግኘት እየተቸገሩ መሆናቸውን የገለጹት ካርዲናሉ፥ “በተበላሹ መንገዶች፣ ድልድዮች እና በመካሄድ ላይ ባሉ ግጭቶች ምክንያት ለእነዚህ ማህበረሰቦች የአደጋ ጊዜ እርዳታ ማቅረብ በጣም ከባድ ነበር” ሲሉ አክለዋል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በካሩና ማይናማር የማህበራዊ አገልግሎት (KMSS) ድርጅት በኩል ለተጎዱ ማህበረሰቦች አፋጣኝ የነፍስ አድን እርዳታ ለማድረግ ስትሰራ ቆይታለች።

ይህንንም በማስመልከት ብጹእ ካርዲናል ቦ “ቡድኖቻችን ከፍተኛ አደጋ በደረሰባቸው ከተሞች ውስጥ ከ2,100 በላይ ለሚሆኑ ግለሰቦች የአደጋ ጊዜ የምግብ፣ ውሃ፣ መጠለያ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ የዕርዳታ ቁሳቁሶችን አከፋፍለዋል” ያሉ ሲሆን፥ “በተጨማሪም በህፃናት ጥበቃ እና በስነ-ልቦና ድጋፍ ላይ ትኩረት አድርገናል፣ እንዲሁም የረጅም ጊዜ የማገገም እና የመልሶ ማቋቋም ጥረቶች እቅድ አውጥተናል” ብለዋል። 

ብፁዕ ካርዲናል ቦ እንደገለፁት ሁሉን አቀፍ እና የተደራጀ ምላሽ ለመስጠት ከዓለም አቀፍ እና ከሀገር ውስጥ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር እንዲሁም ከተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎች ጋር በንቃት ተባብረው ሲሰሩ እንደነበርም ጭምር ገልጸዋል።

ከእነዚህም ውስጥ ሲ አር ኤስ( CRS)፣ ትሮኬይር (Trocaire)፣ ካፎድ (CAFOD)፣ ሊፍት(LIFT) እና የመሳሰሉት ድርጅቶች የእርዳታ ጥረቱን ለመደገፍ ወሳኝ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የአደጋ ጊዜ ፍላጎቶችን ለመገምገም፣ ክፍተቶችን ለመጠቆም እና የትብብር እድሎችን ለመፈተሽ በክላስተር-ደረጃ በቅንጅት እየተሳተፉ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ቦ የማይናማር ሕዝብ ይህንን አደጋ ለመጋፈጥ አንድ ሆነው እንዲቆሙ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ “ከአደጋው የማገገም መንገዱ ረጅም እና አድካሚ ይሆናል፥ ነገር ግን በእምነት፣ በርህራሄ እና በጋራ በሚወሰድ እርምጃ እነዚህን ተግዳሮቶች እናሸንፋለን” ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ቦ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማይናማር ሕዝብ ድጋፍና አጋርነት እንዲሰጥ፣ አስቸኳይ የሰብዓዊ ዕርዳታ እና የረዥም ጊዜ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የመቋቋም አቅምን በማጎልበት ላይ አጽንኦት እንዲሰጥ ጥሪ በማቅረብ “በአንድነት ተስፋን ወደነበረበት መመለስ እና በዚህ አደጋ የተጎዱትን ህይወት መለወጥ እንችላለን” በማለት አጠቃለዋል።
 

30 September 2024, 16:42