SAʴý

ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፤ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፤  

ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፥ "የፍቅር ተሐድሶ"

በአሁኑ ጊዜ ረጅም ዕድሜ ሲባል የባለ ትዳሮች ጥብቅና ልዩ ፍቅራዊ ግንኙነቶች ለአራት፣ ለአምስት ወይም ለስድስት አሥርተ ዓመታት መዝለቅ እንዳለባቸው አመላካች ነው። በመሆኑም፣ የመጀመሪያው ውሳኔ የጋብቻ ፍቅር በየጊዜው መታደስ ይኖርበታል። ከጥንዶቹ አንዱ ለሌላው ጥልቅ የሆነ ወሲባዊ ፍላጎት ባይኖረውም እንኳ፣ እርሱ ወይም እርስዋ አሁንም አንዳቸው የአንዳቸው የመሆናቸውን ደስታ ሊያጣጥሙና በሕይወት ውስጥ ያለውን ማንኛውንም ነገር የሚካፈልላቸው “አጋር›” እንዳላቸው እንጂ አንዳቸውም ቢሆኑ ብቸኛ ያለመሆናቸውን ግንዛቤ ሊያዳብሩ ይችላሉ። እርሱ ወይም እርስዋ በሕይወት ጉዞ ላይ አብሮ ተጓዥ፣ የሕይወትን ችግሮችና ከሕይወትም የሚገኘውን ደስታ ተካፋይ ናቸው። ይህ እርካታ ለጋብቻ ፍቅር የተገባ የመዋደድ አካል ነው። ዕድሜ ልክ ተመሳሳይ ስሜት ይኖረናል የሚል ዋስትና የለም። ሆኖም ባልና ሚስት የሚጋሩት ለዕድሜ ልክ የሚዘልቅ ዕቅድ ካላቸው፣ እርስ በርስ መዋደድና ሞት እስኪለያቸው ድረስ ገንቢ ቅርበት ፈጥረው በአንድነት መኖር ይችላሉ። እነርሱ ቃል የሚገቡት ፍቅር ከማናቸውም ጥልቅ ስሜት ወይም እነዚህን ሁሉ ከሚያካትት የአስተሳሰብ ሁኔታ የላቀ ነው። ጥልቅ ፍቅርና ልባዊ የሆነ የዕድሜ ልክ ውሳኔ ነው። ያልተፈቱ ግጭቶችና የሚያደናግሩ ስሜታዊ ሁኔታዎች ቢኖሩም፣ ጥንዶቹ የመውደድ፣ አንዳቸው የአንዳቸው የመሆን፣ ሕይወታቸውን የመጋራት እንዲሁም በፍቅራቸውና በይቅርታቸው የመቀጠል ውሳኔአቸውን በየዕለቱ ያድሱታል። እያንዳንዳቸው በራስ የዕድገትና የሕንጸት ጎዳና ወደ ፊት ይራመዳሉ። በዚህ ጉዞ ላይ ፍቅር በእያንዳንዱ እርምጃና አዲስ ደረጃ ደስታን ያገኛል።

በማንኛውም የጋብቻ ሂደት ውስጥ አካላዊ ገጽታዎች ይቀየራሉ፤ ይህ ማለት ግን ፍቅርና መተሳሳብ ይደበዝዛል ማለት አይደለም። ሌላውን ሰው የምንወደው በአካሉ ሳይሆን በማንነቱ ነው። ሰውነት ቢያረጅም፣ ልባችንን የሰረቀውን የመጀመሪያ ማንነቱን አሁንም ያሳያል። ሌሎች ያንን ውበት ማየት ቢሳናቸውም፣ የትዳር አጋር ግን በፍቅር ዐይን ማየቱን ስለሚቀጥል የእርሱ ወይም የእርስዋ ፍቅር አይቀንስም። እርሱ ወይም እርስዋ አንዱ የሌላው መሆናቸውን ዳግመኛ ያረጋግጣሉ፣ ያንንም ምርጫ በታማኝነትና በፍቅራዊ ቅርበት ይገልጹታል። እነርሱም የጋብቻ ተልእኮአቸውን ሲፈጽሙ፣ የዚህ ምርጫ ክቡርነት፣ በጥልቀቱና በስፋቱ፣ ለአዲስ ዐይነት ስሜት ያነሣሣቸዋል። ምክንያቱም “እንደ ሰው በሌላ ሰው የሚቀሰቀስ ውስጣዊ ስሜት… በራሱ ወደ ወሲባዊ ድርጊት አያመራም”። ሌላ ትርጉም ያላቸው መገለጫዎችም ይኖሩታል። በእርግጥ ፍቅር ‹‹ብቸኛ እውነታ ቢሆንም፣ የተለያዩ ገጽታዎች ያሉትና በተለያዩ ጊዜያት፣ አንዱ ወይም ሌላው ገጽታው ይበልጥ ጎልቶ ሊወጣ የሚችል ነው”። የጋብቻ ትስስር አዲስ መገለጫዎች ይኖሩታል፣ በቀጣይነት እንዲጠነክርም አዳዲስ ዘዴዎች ያስፈልጉታል። እነዚህም ዘዴዎች ትስስሩን ለመጠበቅም ለማጠንከርም የሚረዱና የየዕለት ጥረትን የሚጠይቁ ናቸው። ሆኖም ይህ ሁሉ ሊሳካ የሚችለው፣ ጸጋውን እንዲያፈስ፣ በእያንዳንዱ አዲስ ሁኔታ ውስጥ ፍቅራችንን እንዲያጸና፣ እንዲመራና እንዲያድስ መለኮታዊ ብርታቱንና መንፈሳዊ እሳቱን እንዲያወርድ ወደ መንፈስ ቅዱስ ስንጸልይ ነው።

ምንጭ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 163-164 ላይ የተወሰደመሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።

አዘጋጅ አባ ዳንኤል ኃይለ
 

21 September 2024, 16:10