SAʴý

ብጹዕ ካርዲናል ኢግኔሽየስ ሱሃርዮ ለአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች መግለጫ ሲሰጡ፥ ብጹዕ ካርዲናል ኢግኔሽየስ ሱሃርዮ ለአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች መግለጫ ሲሰጡ፥  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በኢንዶኔዥያ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የተስፋ ብርሃን እንደሚሆን ተገለጸ

የኢንዶኔዥያው ጳጳሳ ብጹዕ ካርዲናል ኢግኔሽየስ ሱሃርዮ ለአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በሰጡት መግለጫ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢንዶኔዢያ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በሃይማኖቶች መካከል አንድነትን በማጎልበት የተስፋ ብርሃን ይሆናል በማለት ገልጸውታል። ብጹዕነታቸው ይህን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢንዶኔዥያ ሐዋርያዊ ጉብኝት ከማድረጋቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ኢግኔሽየስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ኢንዶኔዥያ መዲና ጃካርታ ከመምጣታቸው ጥቂት ቀናት በፊት ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ለተውጣጡ ጋዜጠኞች ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

የጃካርታ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ኢግኔሽየስ ሐሙስ ነሐሴ 23/2016 ዓ. ም. ለጋዜጠኞቹ ባደረጉት ገለጻ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው በተለያዩ የሃይማኖት ቡድኖች መካከል መልካም ግንኙነትን ለማስፈን ያላቸውን ቁርጠኝነት በማጉላት በማኅበረሰቦችም መካከል ግንኝነትን ለመገንባት ለሚያደርጉት ጥረት አጽንኦት ሰጥተዋል።

የቅዱስነታቸው የተስፋ መልዕክት፣ ብጹዕ ካርዲናል ሱሃርዮ እንደገለጹት፥ በዓለም ትልቁ የእስልምና እምነት ተከታይ ቁጥር በሚገኝባት እና በሃይማኖቶች መካከል በመቻቻል ትውፊቷ በምትታወቅ ኢንዶኔዥያ ውስጥ በጥልቅ እንደሚያስተጋባ ገልጸዋል።

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት ቀደም ብሎ ታዋቂው የኢንዶኔዥያ ሙስሊሞች ቡድን “ለመንፈሳዊ የተስፋ ተጓዥ ሰላም ይሁን!” በሚል ርዕሥ በቅርቡ የሳተመው መጽሐፍ ከአስገራሚ ነገሮች መካከል አንዱ እንደ ሆነ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ኢግኔሽየስ ገልጸዋል።

ብጹዕነታቸው በማከልም ይህ በርካታ ታዋቂ የኢንዶኔዥያ ሙስሊሞች ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያላቸውን ክብር እና አድናቆት የሚያጎላ እንደሆነ አስረድተው፥ በርካታ የኢንዶኔዥያ ታዋቂ ሙስሊሞች በኅብረት የፃፉት መጽሐፍ ባልጠበቀ ሁኔታ እንዳስገረማቸው አስረድተዋል።

በተለይ በሃይማኖቶች መካከል በመደረግ ላይ ባለው ውይይት እና ትብብር ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን የተስፋ ምልክት አድርገው በመቀበላቸው ደራሲያንን አመስግነው፥ የመጽሐፉ መታተም በቫቲካን እና በኢንዶኔዥያ ሙስሊም ማኅበረሰብ መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት የሚያንፀባርቅ እንደሆነም ብጹዕ ካርዲናል ሱሃርዮ አብራርተዋል።

የኢንዶኔዥያ ሙስሊሞች “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚለውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን እና የአቡ ዳቢ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሠነድ መርሆችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያደርጉትን ጥረት ቅድስት መንበር እንደ አርአያነት እንደምትመለከተው ገልጸው እነዚህ ሁለቱም ሠነዶች በተለያዩ እምነቶች መካከል በሰላም አብሮ መኖርን የሚደግፉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዚህ በፊት ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በመስከረም ወር 2020 ዓ. ም. በኢንዶኔዥያ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ አቅደው የነበረ ቢሆንም በ COVID-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለሌላ ጊዜ በማዛወር በጉጉት ሲጠብቁት እንደ ነበር ተነግሯል።

ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ኢግኔሽየስ በማብራሪያቸው፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢንዶኔዥያ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት አንዱ ትኩረት በጃካርታ ጄሎራ ቡንግ ካርኖ ስታዲየም ነሐሴ 30/2016 ዓ. ም. 88,000 ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቀው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት እንደሆነ ተናግረዋል።

በዚህ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ 800 ካህናት፣ ሁለት የኢንዶኔዥያ ብጹዓን ካርዲናሎች፣ 34 ብጹዓን ጳጳሳት፣ ከእስያ አኅጉር የመጡ አሥር ብጹዓን ጳጳሳት እና አንድ የአውስትራሊያ ጳጳስ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከቦታ ስፋት ውስንነት ምክንያት ሥነ-ሥርዓቱ ለጃካርታ ሀገረ ስብከት እና በውስጡ ለሚገኙ ቁምስናዎች ምዕመናን በመገናኛ ብዙሃን በኩል በቀጥታ እንደተላለፍላቸው ታውቋል።

አዘጋጅ ኮሚቴውን የሚመሩት የቀድሞው የኢንዶኔዥያ ትራንስፖርት ሚኒስትር አቶ ኢግኔሽየስ ዮናን የታዳሚዎችን ፍሰት ለመቆጣጠር በጃካርታ ባለስልጣናት የተሰጣቸውን ምክር ጨምሮ ዝግጅቱ በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲፈፀም ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠዋል።

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ከሮም የሚመጡ ጋዜጠኞችን ጨምሮ ከ 700 የሚበልጡ የኢንዶኔዥያ ጋዜጠኞች ዝግጅቱን የሚዘገቡ ሲሆን፥ የቅዱስነታቸው ታሪካዊ ጉብኝት በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚዲያ ትኩረትን ይስባል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢንዶኔዥያ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብጹዕ አቡነ አንቶኒየስ ሱቢያንቶ ቡንጃሚን፥ ይህን ብሔራዊ ዝግጅት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በሰላም እንዲፈጸም ለጣሩት የኢንዶኔዥያ ማዕከላዊ መንግሥት፣ የጃካርታ ከተማ ባለሥልጣን፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ የቅድስት መንበር እንደራሴ ጽሕፈት ቤት እና መቶ የሚሆኑ በጎ ፈቃደኞችን በሙሉ ከልብ አመስግነዋል።

 

31 August 2024, 15:51