SAʴý

2022.09.30 Sunday Gospel Reflections

የኅዳር 16/2016 ዓ.ም የ33ኛው እለተ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

“እግዚአብሔርን በማመን ስጦታውን መጠቀም ይገባል”!

የእለቱ ንባባት

1.      መ. ምሳሌ 31፡10-13.19-20.30-31

2.     መዝሙር 127

3.     1 ተሰሎንቆ 5፡1-6

4.    ማቴዎስ 25፡14-30

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የሰነፉ አገልጋይ ምሳሌ

 

“የእግዚአብሔር መንግሥት አገልጋዮቹን ጠርቶ ያለውን ንብረት በዐደራ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ሊሄድ የተነሣ አንድ ሰውን ትመስላለች፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው በመደልደል ለአንዱ አምስት ታላንት፣ ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ ታላንት ሰጥቶ ጕዞውን ቀጠለ። አምስት ታላንት የተቀበለው ሰውየ፣ ወዲያው በገንዘቡ ንግድ ጀምሮ አምስት ታላንት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው ሁለት አተረፈ፤ አንድ ታላንት የተቀበለው ግን መሬት ቈፍሮ የጌታውን ገንዘብ ደበቀ።

“የአገልጋዮቹም ጌታ ከብዙ ጊዜ በኋላ ከሄደበት ተመልሶ የሰጣቸውን ገንዘብ ተሳሰበ። አምስት ታላንት የተቀበለውም፣ ሌላ አምስት ተጨማሪ ታላንት ይዞ በመቅረብ፣ ‘ጌታ ሆይ! አምስት ታላንት ዐደራ ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸውልህ አምስት ተጨማሪ ታላንት አትርፌአለሁ’ አለው።

“ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። “እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ሁለት ታላንት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸው ሁለት ተጨማሪ ታላንት አትርፌአለሁ’ አለው።

“ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። “አንድ ታላንት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ ፈራሁህ፤ ሄጄም መሬት ቈፍሬ ታላንትህን ጕድጓድ ውስጥ ደበቅሁት፤ ገንዘብህ ይኸውልህ’ አለው።

“ጌታውም መልሶ፣ ‘አንተ ክፉ፣ ሰነፍ አገልጋይ፤ ካልዘራሁበት የማጭድ፣ ካልበተንሁበትም የምሰበስብ መሆኔን ታውቅ ኖሯል? ታዲያ፣ በምመለስበት ጊዜ ገንዘቤን ከነወለዱ እንዳገኘው ለለዋጮች መስጠት ይገባህ ነበር።

“ ‘በሉ እንግዲህ ታላንቱን ወስዳችሁ ዐሥር ታላንት ላለው ስጡ፤ ላለው ይጨመርለታል፤ የተትረፈረፈም ይኖረዋል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ይህን የማይረባ አገልጋይ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት’ አለ።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ! ከማቴ. 25፡14-30 ተወዶ የተነበበው የዕለቱ ቅዱስ ወንጌል ስለ መክሊቶቹ ምሳሌ ይናገረናል። ለጉዞ የወጣ አንድ ጌታ መክሊቶቹን ወይም ንብረቶቹን ለአገልጋዮቹ በአደራ ይሰጣል። የገንዘብ መክሊቶች ነበሩ። ለእያንዳንዳቸው በችሎታቸው መጠን ከፋፍሎ ሰጣቸው። ከሄደበት በተመለሰ ጊዜ ምን ያህል እንዳተረፉ ጠየቃቸው። ከመካከላቸው ሁለቱ የተቀበሉትን በእጥፍ አሳድገው ሰጡት፤ ጌታውም አመሰገናቸው። ነገር ግን ሦስተኛው በፍርሃት የተነሳ መክሊቱን ቀብሮት ስለነበር ምንም ሳያተርፍበት ከቀበረበት አውጥቶ ያለ ትርፍ መልሶ ሰጠው። በዚህም ምክንያት በከባድ ሁኔታ ገሰጸው። ይህን ምሳሌ ስንመለከት፣ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ የምንቀርብባቸውን ሁለት የተለያዩ መንገዶች መማር እንችላለን።

የመጀመሪያው መንገድ፥ የተቀበለውን መክሊት የሚቀብር፣ እግዚአብሔር የሰጠውን ሃብት ማየት የማይችል ሰው ነው። ይህ ሰው በጌታውም ሆነ በራሱ የማይታመን ነው። ለጌታውም እንዲህ አለው፡- “ጌታ ሆይ! ካልዘራህበት የምታጭድ እና ካልበተንህበት የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደሆንክ አውቃለሁ” (ማቴ. 25:24)። ይህ ሰው ጌታውን የሚፈራ ሰው ነበር። ሊሰጠው የነበረውን ክብር ያልተመለከተ፣ ጌታው በእርሱ ላይ የጣለውን አደራንም ያልተመለከተ ነገር ግን ከሚሰጠው በላይ የሚጠይቅ ጌታ መሆኑን ብቻ ተመለከተ። ይህ ሰው ለእግዚአብሔርም ያለው አመለካከት ይህን ይመስላል። በቸርነቱ ማመን አይችልም፤ እግዚአብሔር ለእርሱ ያለውን ቸርነትንም ማመን አይችልም። በተቀበለው ተልዕኮ ውስጥ እራሱን ለመሳተፍ የልፈቀደውም ለዚህ ነው።

በሁለተኛው መንገድ፥ ሌሎቹን ሁለት ዋና ገጸ-ባህሪያት ስንመለከት፥ በአደራ የተጣቸውን መክሊት በእርሱ ላይ ባላቸው እምነት መልሰው ሲከፍሉት እናያለን። እነዚህ ሁለቱ አገልጋዮች የተቀበሉትን ሁሉ ሥራ ላይ በማዋል፥ ምንም እንኳን መጀመሪያ ላይ ሁሉም ነገር መልካም እንደሚሆን ባያውቁም ጥናት ያደርጉ ነበር። የተለያዩ ዕድሎችን ይመለከቱ እና በጥበብ መልካም የሚሆነውን መንገድ ይፈልጉ ነበር። አደጋ እንደሚኖረው ቢያውቁም ሊጋፈጡ እራሳቸውን ዝግጁ ያደረጉ ናቸው። ይተማመናሉ፣ ሁኔታውን በሚገባ ያጠናሉ፤ አደጋ ሊደርስ እንደሚችልም ያውቃሉ።  ስለዚህ፣ በነጻነት እና በጥበብ በመሥራት አዲስ ሃብት ለማፍራት ድፍረት አላቸው (ማቴ. 25: 20-23)።

ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ከእግዚአብሔር ጋር የምንጋፈጠው ይህ መስቀለኛ መንገድ ነው። እግዚአብሔርን መፍራት ወይም ወይም በእርሱ መታመን የሚሉት ናቸው። እንደ ምሳሌው ዋና ተዋናዮች፥ ሁላችንም ተሰጥኦዎችን ተቀብለናል። ሁላችንም ከገንዘብ የምምንበልጥ ውድ የሆንን ነን። ነገር ግን አብዛኛው ሥራችን እና ጥረታችን በእግዚአብሔር ባለን እምነት ላይ የተመካ ነው። ይህም ልባችንን ነጻ በሚያወጣው፣ በጥበብ በተሞላ የመልካም ሥራ ፈጻሚዎች እንድንሆን ያደርገናል። እምነት ነፃ እንደሚያወጣን ሁልጊዜ ማስታወስ ይገባል። ፍርሃት ግን ሽባ ያደርገናል። ይህን በልጆች የትምህርት ሕይወት ላይ እናያለን። ስለዚህ እራሳችንን እንጠይቅ፡- እግዚአብሔር አባት እንደሆነ እና እኔን ስለሚያምነኝ ስጦታዎችን በአደራ እንደሰጠኝ አምናለሁ? በውጤቶች እርግጠኛ ባልሆን ወይም በቀላል የማይገኙ ባሆኑም ራሴን ለሥራ እስከማሰማራ ድረስ በእርሱ እታመናለሁ? በየቀኑ በጸሎት ‘ጌታ ሆይ! በአንተ ታምኛለሁ፣ በሥራዬ እንድቀጥል ብርታትን ስጠኝ’ ማለት እችላለሁን? የሰጠኸኝ ነገሮች በሙሉ ወደፊት የምወስድበትን መንገድ አሳውቀኝ” እላለሁ?

በመጨረሻም፣ እንደ ቤተ ክርስቲያን፥ በመካከላችን እርስ በእርስ የመተማመን፣ የመከባበር፣ በአንድነት ለመራመድ የሚረዳንን፣ እራሳችንን ለሌሎች ክፍት የሚያደርግ እና በሰዎች መካከል ፍቅርን የሚያነቃቃ ሁኔታ እናዳብራለን? እስቲ በዚህ ላይ እናስብበት። ፍርሃትን እንድናሸንፍ፣ እግዚአብሔርን ፈጽሞ ሳንፈራ እምነታችንን በእርሱ ላይ እንድናስቀምጥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን”።

NJͭ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኅዳር 9/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በዕለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው ካደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የተወሰደ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

25 November 2023, 21:12