SAʴý

ሊቀ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል  

ቅዱስ ሚካኤል ጠባቂ መልአክት

ሕዝበ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር እናት ቀጥሎ ከመላእክትና ከቅዱሳን ሁሉ ቅዱስ ሚካኤልን እጅግ ያከብራል አማላጅነቱን ይማጠናል። ብዙ የሚያከበረው ስለሆነ በየወሩ ከፍ ባለ መንፈሳዊነት ዝክር ስሙ ይወደሳል። በኀዳር 12 ቀን መጽሐፍ ስንከሳር ስለ ቅዱስ ሚካኤል “ይህ ቀን የቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት የሠራዊት መላክት ሁሉ ዋና አዛዥ ዝክር ነው፡፡ በልዑል እግዚአብሔር መንበር ፊት ቆሞ ስለ ሰዎች ይማልዳል» (መጽ. ስንክ. ኀዳር 12 ቀን) ይላል፡፡

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ሚካኤል ማለት “ማን እንደ እግዚአብሔር” ማለት ነው፡፡ የዚህን ክቡር ስም ታሪክ እንድናውቅ፣ የቅዱስ ሚካኤል ትልቅነት እንድነገነዘብ በሐሳባችን ወደ አሳዛኝ የመላእክት ውድቀት መመልከትና ወደ ኋላ መለስ ብለን ማየት ያስፈልገናል፡፡ እግዚአብሔር መላእክትን ከፈጠራቸው በኋላ እምነታቸውን ለማወቅ ለጥቂት ጊዜ ከፊታቸው ተሰወረ፡፡ ያን ጊዜ ከመላእክት አንዱ የነበረው ሳጥናኤል እግዚአብሔር የሌለ መስሎት ፈጣሪው የማያየው መስሎት ፍጡር መሆኑን ረስቶ እንደ አምላከ ፈጣሪ መሆንን ተመኘ፡፡ እግዚአብሔርን ማገልገል አልፈልግም እምቢ አልታዘዝም ወንበሬንም ከሰማይ በላይ በከዋክብት መካከል አስቀምጣለሁ፣ እንደ ልዑልም እሆናለሁ፣ እርሱን እመስላለሁ፣ ከእርሱ ጋር እኩል ሆኜ እስተካከላለሁ ... ወዘተ. እያለ በትዕቢት ተሞልቶ የሚያዋጣውን አምላክን ካደ፡፡ እንደ ፈጣሪው አምላክ ሥልጣን ለመጨበጥ ሞከረ፡፡ መጥፎውን አብነቱን ብዙዎች መላእክት ተከተሉትና አብረውት ከእርሱ ጋር ወደቁ፡፡ በዚህ ዓይነት በፈጣሪያቸው ፊት ይህ ነው የማይባል ትልቅና አሳፋሪ በደል ፈጸሙ፡፡

ቅዱስ ሚካኤል ግን በቁጥር ከሽፍቶቹ እጅግ በሚበልጡ ጀግና ታማኝ መላእክት ጋር ሆኖ እነርሱን በመምራት ከዚህ አስነዋሪ ኃጢአትና በደል ፈተናውን በማሸነፍ ከዚህ አስከፊ ከህደት ነጻ ሆኖ በአምላኩና በፈጣሪው እመነት ጸንቶ ኖረ፡፡ “ራሱን ዝቅ አድርጐና ተንበርክኮ ለፈጣሪው ሰገደና አመለከ»(ዋዜማ ዘቅዱስ ሚካኤል)፡፡

ይህ ብቻ አይደለም የቅዱስ ሚካኤልን ትሕትናና ቅድስና የሚገልጥና የሚያንጸባርቅ ከዚህ ሌላም የሳጥናኤልና የግብረ አበሮቹ ሽፍቶች መላእከት ትዕቢትና ክህደት እጅግ አስቆጥቶት በዚህ አኳያ በአምላክ ፍቅር ተቃጥሎ “ማን ነው እንደእግዚአብሔር ፈጣሪና ልዑል አምላክ!” እያለ ፎክሮ ከሃዲ ጠላቱን ሊዋጋ ተነሳ። ያን ጊዜ ታላቅ ጦርነት ተቀሰቀስና ሚካኤልና የእርሱ ታማኝ መላእከት በዘንዶ ከተመሰለው ሰይጣንና ከተከታዮቹ ጋር አመጸኞችና ሽፍቶች መላእክት ጋር ከባድ ጦርነት ገጠሙና ዲያብሎስና ጓደኞቹ ተሸነፋ፡፡ ዲያብሎስና ግብረአበሮቹ ከመንግስተ ሰማያት ወደ ምድር ወደ ገሃነመ እሳት ተጣሉ፣ ለዘለዓለም ከሰማይ ተባረሩ፣ በዚህ ሁኔታ ለእነርሱ በመንግሥተ ሰማያት ሥፍራም አልተገኘላቸውም» (ራእ. 12፣7)፡፡

ቅዱስ ሚካኤል በአምላክ ኃይልና ሥልጣን ሳጥናኤልን ከግብረ አበሮቹ ጋር ወደ ገሃነመ እሳት ጣላቸው፡፡ “ማን እንደእግዚአብሐር» ብሎ ቅዱስ ሚካኤል ሊቀመላእክት መነሳቱ ታማኝና ትሑት የእግዚአብሔር አገልጋይ መሆኑን አስመስክሯል፡፡ ሳጥናኤል ግን በፈተና ጊዜ እግዚአበሔር ለዘወትር የተሰወረና የሌለ ስለመሰለውና ደፋርም በመሆኑ ካደው፡፡ ፍጡር መሆኑ ተዘንግቶት በአሸዋ የቆመ ዙፋን አበጅቶ ወደ ፈጣሪ ማዕረግ ለመውጣት ፈለገ፡፡ ነገር ግን የአምላክ ማዕረግ ይቅርና ሲፈጥረው የነበረውን የገዛ ራሱን የመላእክት ማዕረግ ተገፎ እርግማኑን ተሸክሞ ለዘለአለም በገሃነመ እሳት ሊሰቃይ ተኰነነ፡፡

ቅዱስ ሚካኤል ግን በፈተና ወቅት እግዚአብሔርን አልካደም፡፡ እርሱ ዘወትር ፍጡር እግዚአብሔር ደግሞ ፈጣሪ እንደሆነ አልካደም እንደሳጥናኤል አልተሳሳተም፡፡ በትሕትና በእምነት እግዚአብሔርን ያገለግል ስለነበረ ተቃዋሚ ሆኖ የተነሣውን ሳጥናኤን በርትቶ ተዋጋው፡፡ እግዚአብሔርም በቅዱስ ሚካኤል ታላቅ ፍቅርና ከፍ ያለ እምነት እጅግ ተደስቶ ሲፈጠር ከነበረው ይበልጥ እጥፍ ድርብ ከብርና ሥልጣን አጐናጸፈው፡፡ የመላእክት ሠራዊት ሁሉ አለቃና ርዕሰ -መላእክት አደረገው፡፡ “መልእክተኛዬ ነህ» (ሰላምታ (መልክዕ) ዘቅዱስ ሚካኤል) አለው! ከመላእከት ሁሉ አብልጦ ወደደው፡፡

“ቅዱስ ሚካኤል ኃይል የሞላበት መልአክ ነው፣ ክቡርና በመንበሩ ልዑል ነው”፡፡ የእግዚአብሔርን አገልጋይና እኛን የሚያንጽ መልካም አብነት ያሳየ መልአክ ነው፡፡ ታማኝነቱ በእምነት የደከምነው እኛን የሚገስጽ ጉልህ አብነት ነው፡፡

ቅዱስ ሚካኤል እግዚአብሔርን ለማገልገል በሰማይ እንደተፈጠረ እንዲሁም እኛ በምድር እግዚአብሔርን ለማገልገል ተፈጥረናል፡፡ስለዚህ እኛም በአምላክ አገልግሎት እንደ እርሱ ትጉሆችና ታማኞች መሆን ይገባናል፡፡ በተለይ በፈተና ጊዜ የእርሱን ጽናትና ብርታት እንድንከተል ያስፈልገናል፡፡ ሰይጣንና ክፋ ሰዎች ፈጣሪያችንን ሊያስክዱን ከእርሱ ሊያርቁንና በእርሱ ምትክ ደግሞ በእኛ ላይ ሊነግሱ ሲፈልጉ እንደ ቅዱስ ሚካኤል “ማን እንደ እግዚአብሔር!» እያልን ጨክነንና በርትተን እንዋጋቸው እንታገላቸው፡፡

ቅዱስ ሚካኤል የአዳም ልጆች ታማኝ ጠባቂና ረዳት ጠባቂ ነው፡፡ “የሰው ዘር ርኀሩኀ መልአክ፣ በልዑል እግዚአብሔር መንበር ፊት ቆሞ ስለ ሰዎች የሚያማልድ ነው፡፡ ይህ ትልቅ መልአክ በሰማይ እግዚአብሔርን ሊነገር በማይቻል ትጋት ያገለግላል፣ በምድር ደግሞ እኛን ሰዎችን ከፍ ባለ ርኀራኄና ጥንቃቄ ይጠብቀናል፡፡ ቀድሞ እስራኤላውያንን በችግራቸው ጊዜ ይረዳቸው ነበር፣ ምክንያቱም መጽሐፍ ድጓን “መልአኩን ልኮ አዳናቸው፣ ሚካኤል በእስራኤል ሠራዊት ፊት ለፊት ይሄድ ነበር” (መጽ.ድጓን) ይላል፡፡ ትንቢተ ዳንኤል “ሕዝብህን የሚጠብቀው ታላቁ መልአክ ሚካኤል በዚያን ጊዜ ይገለጣል” (ዳን.12፣1)ይላል፡፡

ይህ ትልቅ መልአክ ቀድሞ ለእስራኤላውያን ያደርገው የነበረ እርዳታ ዛሬም ለሕዝበ ክርስቲያን እየቀጠለ ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ “ይትዐየን መልአክ እግዚአብሔር ዐውዶሙ ለዕለ ይፈርህዎ ወያድኀኖሙ፡- የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት አጠገብ ሆኖ ይጠብቃቸዋል፣ ከጠላቶቻቸው ደግሞ ያድናቸዋል” (መዝ.33፣7) ይላል፡፡ ሕዘበ ክርስቲያን ቅዱስ ሚካኤል ብዙ እንደሚያምነውና እንደሚያከብረው እንዲሁ እሱ ሕዝበ ክርስቲያንን ብዙ ያፈቅረዋል በልዩ መንገድ ይመለከተዋልና ይጠብቀዋል፡፡ በነፍስም ሆነ በስጋ ይረዳዋል፡፡ በውጊያ ወቅትና በፈተና ጊዜም በጐኑ ይቆማል፡፡

የቅዱስ ሚካኤልን ዕርዳታ እንለምን፤ እግዚአብሔር ቅድስ ሚካኤልን ጠባቂያችንና ረዳታችን አድርጐ ሹሞታል። ይህ መሠረት ያለው ሐቅና እምነት ነው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ክቡርና የትልቅ ሥልጣን ባለቤት ታማኝ መዳኛችንም ነው፡፡ እርሱ ከእኛ ጋር እያለ የሚያስፈራን ነገር የለም፡፡ ሁልጊዜ በተለይም በችግራችን ወቅት እንዲረዳን ወደ እርሱ እንማጸን፡፡ ጌታ የሰጠን ትልቅ ጠባቂ መልአክ በመሆኑ “ቅዱስ ሚካኤል ሆይ ለምንልን» እያልን ጥበቃውን እንጠይቅ፡፡

 

22 November 2023, 14:12