SAʴý

ሊቀ ጳጳስ ሊ ሻን ከካርዲናል ቾው ኢ ቶንግ ጋር በመሆን በሆንግ ኮንግ ካቴድራል ሥርዓተ ቅዳሴ ሲያሳርጉ ሊቀ ጳጳስ ሊ ሻን ከካርዲናል ቾው ኢ ቶንግ ጋር በመሆን በሆንግ ኮንግ ካቴድራል ሥርዓተ ቅዳሴ ሲያሳርጉ 

የቤጂንግ ሊቀ ጳጳስ “በወንድማማችነት መንፈስ” ሆንግ ኮንግን ጎበኙ

የቤጂንግ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ሊ ሻን የካርዲናል ቾውን ግብዣ ተቀብለው ሆንግ ኮንግን ጎብኝተዋል፥ የጉብኝቱም ዓላማ የወንድማማችነት እና የአንድነትን መንፈስ ለማዳበር እንደሆነ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የቤጂንግ ሊቀ ጳጳስ ጆሴፍ ሊ ሻን በሆንግ ኮንግ ሀገረ ስብከት ከህዳር 03 እስከ 05, 2016 ዓ.ም. ድርስ ወንድማማዊነትን የሚያጠናክር እና ጠቃሚ የሆነ ጉብኝት አድርገዋል። ሊቀ ጳጳሱ ከነልዑኮቻቸው ሆንግ ኮንግን እንዲጎበኙ የተጋበዙት የሆንግ ኮንጉ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል እስጢፋኖስ ቾው ሳኡ-ያን ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ቤጂንግን በጎበኙበት ወቅት ነበር።

ሊ ሻን: ‘ሁልጊዜ አምላክህን አመስግን’

ሊቀ ጳጳስ ሊ ሻን በጉብኝታቸው ወቅት እንደገለፁት፥ ይህ ጉብኝት ይሳካ ዘንድ ብፁዕ ካርዲናል ቾው እንዲሁም ሆንግ ኮንግ ያሉ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ላደረጉት አስተዋጽኦ ልባዊ አድናቆት እንዳላቸው መናገራቸውን የሀገረ ስብከቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

‘በሆንግ ኮንግ ቤተክርስትያን እድገት ብዙ ተምረናል’ ያሉት ሊቀ ጳጳሱ ‘ከዚህ ልምድ ወስደን ቤጂንግ ለሚገኘው የካቶሊክ ማህበረሰብ እድገት ላይ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን’ በማለት ቃል ገብተዋል። ሊቀ ጳጳስ ሊ ሻን አክለው እንደተናገሩት አንድ ሰው የሚያጋጥመው ችግር ምንም ይሁን ምን ሁሉም ሰው “ታማኝ እና አምላኩን በማስደሰት እንዲሁም ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን እያመሰገነ እንዲቀጥል” አበረታተዋል።

ቾው፡ ‘እንደ ድልድይ የምታገለግል የሆንግ ኮንግ ቤተክርስቲያን’

ካርዲናል ቾው አንድ ቀን ሁሉም የቻይና ካቶሊኮች በአንድነት ተሰባስበው መጸለይ እንደሚችሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ብጹእ ካርዲናሉ በቅርቡ በተካሄደው የብፁዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ውስጥ ስላደረጉት ተሳትፎ ሲገልፁ፥ የአንድነት ዋና ተዋናይ መንፈስ ቅዱስ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት፥ የሆንግ ኮንግ ሀገረ ስብከት ሚና “እንደ ድልድይ የምታገለግል ቤተ ክርስቲያን” እንደሆነች ደጋግመው ተናግረዋል።

ካርዲናሉ ‘ይህች ቤተክርስቲያን ሁል ጊዜ ሰዎችን አንድ የሚያደርጉ እና የሚያገናኙ ነጥቦች በመፈለግ፥ አዘውትረው የሚመጡትን ልዩነቶች እና ውጥረቶችን በአዎንታዊ መልኩ እየተመለከተች ከወንድሞቿ እና እህቶቿ ጋር መጓዝ አለባት’ ብለዋል።

የጉብኝቱ ሂደቶች

ጉብኝቱ የተጀመረው ህዳር 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕለተ ሰኞ ሲሆን፥ በሀገረ ስብከቱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በጋራ የምሽት ጸሎት ሥነ ስርዓት በማድረግ ነበር። ከዚያም በብጹዕ ካርዲናል ቾው ቢሮ ውስጥ የስጦታ ልውውጥ ተደርጓል። በዚህም መርሃግብር የቤጂንግ ሊቀ ጳጳስ ለካዲናሉ መስታወት ላይ የተሳለ የጄሱሳዊው ሚሲዮናዊ ማትዮ ሪቺን ምስል ሲሰጡ፥ ብፁዕ ካርዲናል በበኩላቸው ለሊቀ ጳጳስ ሊ ሻን በነጭ የእንጨት ሰሌዳ ላይ የተሳለ የቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስን ምስል አበርክተዋል።

በማግስቱ ህዳር 4፣ ዕለተ ማክሰኞ የቤጂንግ ልዑካን ወንጌልን ወደ ቻይና ያመጡትን ሚስዮናውያን ሁሉ ለማሰብ የ ‘ንጽህት ድንግል ማሪያም ካቴድራል’ን እንዲሁም የቻይናውያን ሰማዕታት ጸሎት ቤትን ጎብኝተዋል። ከሰዓት በኋላ ሊቀ ጳጳስ ሊ የሆሊ ስፕሪት ሴሚናሪን እና የሆሊ ስፕሪት ጥናት ማእከልን ጎብኝተዋል።

ጉብኝቱ በመቀጠል ህዳር 5፥ ዕለተ ረቡዕ በ‘ንጽህት ድንግል ማሪያም ካቴድራል’ ውስጥ የቅዳሴ ሥነ ስርዓት ተካሂዷል። ፊደስ የዜና አገልግሎት እንደዘገበው ሊቀ ጳጳስ ሊ ሻን የቀድሞው የሆንግ ኮንግ ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ብፁዕ ካርዲናል ጆን ቶንግ እና ከብጹእ ካርዲናል ቻው ጋር በነበራቸው ቆይታ በጣም ደስተኛ እንደነበሩ ገልጿል።

ጉብኝቱ “የሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያን እና ቻይና ውስጥ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን፥ ሕብረት፣ ተሳትፎ፣ ተልእኮ” በሚል መሪ ቃል በተካሄደ ነገረ መለኮታዊ ጉባኤ ተጠናቋል።
 

20 November 2023, 14:17